ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ያደረገው ዝግጅት የሚደነቅ ነው- ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን የድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ያደረገው ዝግጅት የሚደነቅ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለድጋሚና ቀሪ ምርጫ የማስፈጸሚያ ቁሳቁሶችን በማሟላት የፊታችን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በዚህ ረገድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያደረገውን ዝግጅት በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገምግሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ 6ኛውን ድጋሚና ቀሪ ምርጫ ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በሁለት ዙሮች ሀገራዊ ምርጫ ማካሄዱን አስታውሰው፤ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት በጸጥታ እና ተዓማኒነት ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።



 

በዚህም የበጀት ዝግጅትና የጊዜ ሠሌዳ ማውጣት፣ ምርጫ አስፈጻሚ መረጣና ጽሕፈት ቤት የማደራጀት፣ የጸጥታ ስጋት ዳሰሳ፣ የመራጭና ዕጩ ምዝገባ ጨምሮ የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

የድጋሚና ቀሪ ምርጫውንም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በ29 የምርጫ ክልልና በ1 ሺህ 258 የምርጫ ጣቢያ ማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በድጋሚና ቀሪ ምርጫው ከ1 ሚሊየን በላይ መራጮች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የድጋሚና ቀሪ ምርጫው በአራቱም ክልሎች የፊታችን እሁድ ይካሄዳል ነው ያሉት። 

ለዚህም የምርጫ ድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን ምስጢራዊነት በጠበቀ መልኩ በማሳተም አሁን ላይ በየምርጫ ክልሎች በማድረስ በጣቢያዎች የማሠራጨት ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዛራ ቢፍቱሕ፤ የምርጫ ዝግጅትና አፈጻጸምን አስመልክቶ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን አስተያየትና ጥያቄ በጽሑፍ አቅርበዋል።




በተያዘው ዓመት በስድስት ክልሎች በሚደራጁ በ96 ምርጫ ክልሎች የድጋሚና ቀሪ ምርጫን ለማካሄድ የያዘውን ዕቅድ ማሳካት ያልቻለበትን ምክንያት ጠይቀዋል።

በዚህ ሂደትም በአራት ክልሎች በተደራጁ 29 ምርጫ ክልሎች የድጋሚና ቀሪ ምርጫን በተዓማኒነት ለማረጋገጥና የመራጮች ግንዛቤ ማሳደግን አስመልክቶ ጥያቄ አቅርበዋል። 

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ቀደም ሲል 6ኛውን የድጋሚና ቀሪ ምርጫ በስድስት ክልሎች ለማካሄድ ዕቅድ ተይዞ እንደነበር አንስተዋል።

አስቻይ ሁኔታ የሌለባቸውን ሁለት ክልሎች በመቀነስ አሁን ላይ በአራት ክልሎች በ29 የምርጫ ክልልና በ1 ሺህ 258 የምርጫ ጣቢያዎች ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።

የምርጫ ሂደቱን በተዓማኒነት ማካሄድ የሚያስችል መስፈርትን የተከተለ የምርጫ አስፈጻሚ ምልመላ በማካሄድ ገለልተኝነት የማረጋገጥና ሥልጠና የመስጠት ሥራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ፤ ምርጫ ዜጎች የሚያስተዳድራቸውን አካል የሚመርጡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት መገለጫ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በማብቃት ዜጎች በምርጫ ጉዳይ የተሻለ ግንዛቤ የሚይዙበትን ትምህርት ተደራሽ ማድረግ እንደሚኖርበት ገልፀዋል።

በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ ቦርዱ የማስፈጸም አቅሙን ለማሳደግ የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ማዋሉን አድንቀዋል።

 
 

በቀጣይም የመራጮች የስነ-ምግባር ትምህርትና ሥልጠና በማስቀጠል በሃሳብ የበላይነት የተመሠረተ የምርጫ ፉክክርና ምኅዳር እንዲፈጠር አበክሮ መሥራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

የጸጥታ ስጋትና የመንገድ መሠረተ-ልማት ችግሮችን በመቋቋም 6ኛውን የድጋሚና ቀሪ ምርጫን በስኬት ለማካሄድ የተደረገው ዝግጅትም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የምርጫን ተዓማኒነት በማሳጣት ለድጋሚ ምርጫ ምክንያት የሆኑ አካላትን ተጠያቂ በማድረግ ለቀጣይ ሥራ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም እንዲሁ።

 በምርጫ ሂደቱ ላይ 6 ሺህ 380 ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚን በማሰማራት በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤት የሚወከሉ ወንድ 304፤ ሴት 76 በድምሩ 380 ዕጩዎች እንደተመዘገቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም