ቀጥታ፡

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ያለውን የቴክኖሎጂና የፈጠራ አቅም ለማጎልበት እየሰራ ነው

ጂንካ ፤ ሰኔ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ያለውን የቴክኖሎጂና የፈጠራ አቅም ለማጎልበት የመደገፍና የማብቃት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ ።

ዩኒቨርሲቲው ከአሪ ዞን ሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀውና ለሁለት ቀናት የሚቆይ የፈጠራ ሥራዎች ዐውደ ርዕይ ዛሬ  በጂንካ ተከፍቷል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ ዓለሙ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከሚሰራባቸው የትኩረት መስኮች አንዱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው።

በዚህም  ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቃሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ በማበልፀግና በማስተዋወቅ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩትን አካላት እያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሪ ዞን ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የፈጠራ አቅም ያላቸውን ከ20 በላይ ተማሪዎች በመመልመል በሳይንስና በፈጠራ ስራዎች ላይ ተግባር ተኮር ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮን የሚያቀሉ የፈጠራ ሥራዎች እያወጣ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኤልያስ፤ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተው ጥቅም ላይ ከዋሉት ውስጥ የመኖ ማቀነባበሪያና የበቆሎ መፈልፈያ መሣሪያዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሙከራ ደረጃ የተመረቱትን መሣሪያዎች በቀጣይ በብዛት በማምረት ጥቅም ላይ እንዲውሉም ይሰራል ብለዋል።

የአሪ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሉቃስ ቡሪ መምሪያው ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎችን እያበረታታና እየደገፈ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዐውደ ርዕይም የፈጠራ አቅም ለማጎልበትና ለላቀ ፈጠራ ለማነሳሳት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዐውደ ርዕዩ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍሬው አድማሱ ቢሮው በክልሉ ያለውን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፈጠራ ሀሳቦች ወደ  ተግባር እንዲመነዘሩም ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

በዐውደ ርዕዩ የቀረቡት የፈጠራ ሥራዎች በክልሉ የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎች ለማውጣት  የሚያስችል አቅም መኖሩን  እንደሚያመለክትም ተናግረዋል።

በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት መካከል ባለፉት አራት ወራት በፈጠራ ሥራዎች ላይ ተግባራዊ ልምምድ ያደረጉ ተማሪዎች የሰሯቸው ድሮን፣ የውሃ መሳቢያ ሞተር፣ የቆሻሻ ማፅጃና ፕሮጀክተር ይገኙበታል።

በተጨማሪም በግለሰቦችና በተቋማት የተሰሩ ከዕፅዋት የተቀመሙ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎች፣ ውበት መጠበቂያ ሳሙናዎች፣ ደህንነት መጠበቂያ ካሜራዎች፣ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ አምፑሎች፣ ቡና መቁያ ማሽኖችና ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችም ቀርበዋል።

በዐውደ ርዕዩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች የአመራር አባላትና የፈጠራ ባለቤቶች ተገኝተዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም