አገልግሎቱ በአዳማ ቅርንጫፍ የመድኃኒት አቅርቦትን ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርግ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ በአዳማ ቅርንጫፍ የመድኃኒት አቅርቦትን ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርግ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ አደረገ

አዳማ፤ ሰኔ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በአዳማ ቅርንጫፍ የመድኃኒት አቅርቦትን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያግዝ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን አስታወቀ።
አገልግሎቱ በአዳማ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ ስራ አስጀምሯል።
'ከግሎባል ፈንድ' በተገኘ ገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀው 'ኢንተርፕራዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ' የተሰኘ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት የመድኃኒት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚያግዝ ዲጂታል ዘዴ መሆኑ ተገልጿል።
በእስካሁኑ ሂደትም የዲጂታል አሰራር ስርዓቱ በዋናው መስሪያ ቤት፣ በአዲስ አበባ ሁለት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችና በሀዋሳ ቅርንጫፍ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ መደረጉም ታውቋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የመረጃ ስርዓቱ በመድኃኒት አቅርቦቱ ረገድ ተአማኒነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ዲጂታል የመረጃ ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ነው።
የመረጃ ስርዓቱ ትክክለኛና ህብረተሰቡ የሚፈልገው መድሃኒትና የህክምና ግብዓት በቀላሉ እንዲገኝ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አያይዘውም በዚህ ስራ የኢትዮጵያን የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ወደ ዲጂታል በመለወጥ አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ንጉሴ በበኩላቸው ''ስርዓቱ ጠቅላላ አገልግሎትንና የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ አለው'' ብለዋል።
በዚህም ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት በመገንባት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ስርዓቱ የድርጅቱን ውጤታማነትና የስራ ቅልጥፍና የሚጨምር እንዲሁም የውስጥ ግንኙነት ለማሻሻል የጎላ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
መረጃን በአንድ ቋት በማደራጀት የመረጃ ስርዓቱ ወጥና ተአማኒነት ያለው እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ ቅሬታዎች እንዳይፈጠሩም የሚረዳ ነው ሲሉ ገልፀዋል።