ቀጥታ፡

የመረጃ ኃብቶችን በጥራትና በተደራጀ መልኩ በመሰነድ የሀገር ኃብት ማድረግና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2016 (ኢዜአ)፦ የመረጃ ኃብቶችን በጥራትና በተደራጀ መልኩ በመሰነድ የሀገር ኃብት ማድረግና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት ገለጸ።

የመረጃ ኃብቶችን በማሰባሰብ፣ በማደራጀት፣ በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት የመረጃ ኃብቶች አዘገጃጀት የሕትመት ጥራት እና ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ ተግዳሮትን በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በአገልግሎቱ የመረጃ ኃብቶች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ስለሺ ሽፈራው፤ የመረጃ ኃብቶችን በጥራትና በተደራጀ መልኩ በመሰነድ የሀገር ኃብት ማድረግና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

የሪከርድ ሥራ አመራርና የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት መዛግብትን፣ የጽሑፍ ቅርሶችንና የታተሙ እና ያልታተሙ የመረጃ ውጤቶችን በማሰባሰብና በማደራጀት መጠበቅ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

የጥናትና ምርምር ሥራን በማሳደግ ለትውልድ የማስተላለፍ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚሻም ተናግረዋል።

በተለይም የሕትመት፣ የድምፅና የምስል ኃብቶች በአግባቡና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተሰንደው ሊቀመጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመረጃ ኃብቶችን በማሰባሰብ፣ በማደራጀት፣ በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም