ቀጥታ፡

ተማሪዎችና ወጣቶች በኤች አይቪ/ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ጤና ሚኒስቴር

አዳማ፣ሰኔ 12/2016(ኢዜአ)፡-ተማሪዎችና ወጣቶች በኤች አይ ቪ /ኤድስ ስርጭት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ዲኖችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሳተፉበት በትምህርት ተቋማት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያለመ መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጤና መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አለማየሁ ሁንዱማ እንደገለፁት ተማሪዎችና ወጣቶች ለኤች አይቪ/ኤድስ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።

ወጣቶቹ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት ለኤች አይ ቪ/ኤድስ የሚያጋልጡ በመሆኑ በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ወጣቶች የግንዛቤ ማሳደግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል የመረጃ ፍሰት በማጠናከርና ከመዘናጋት እንዲወጡ በማስቻል ጤንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ከባቢን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በተለይም በትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ የተከፈቱ የጫት፣ የመጠጥና ጭፈራ ቤቶችን ከአካባቢው ማንሳት እንደሚገባ መሪ ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።

ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ሃላፊ አቶ ሐብታሙ ካሣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አሁን ያለው የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተቋማቱ ያለው ቸልተኝነት፣ የመረጃ ተደራሽነት እጥረትና የግንዛቤ ክፍተት ችግሩ እንዲሰፋ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከችግሩ ለመውጣት የተማሪዎችንና ወጣቶች ጤናን ለማረጋገጥና የመማር ማስተማር ሂደቱን የተሳለጠ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

መድረኩ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በጋራ ለመረባረብ ያግዛል ያሉት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምላሽ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደመላሽ ምስጋና ናቸው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ በኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪዎች ስለ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ያላቸው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ተጋላጭነቱ ሰፊ መሆኑን አስታውሰዋል።

በትምህርት ቤቶችና ተቋማት ክበባትን ከማደራጀት ባለፈ፤ በቂ ግንዛቤና ዕውቀት እንዲያገኙ በዘርፉ ከሚሰሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የክርስቲያን በጎ አድራጎት ማህበራት ጥምረት ተወካይ አቶ ንጉሴ ተፈራ በበኩላቸው ወጣቶች በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ አግኝተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ከጤናና ከትምህርት ሚኒስቴሮች ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ወጣት ተማሪዎች፣ የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም