ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ኃይል ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 12/2016(ኢዜአ)፦ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል ኃይል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የ2016 የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ፣ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብሩ "በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከናወን ተገልጿል።

  መርሃ-ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።

የዘንድሮው መርሃ-ግብር በ14 መስኮች አገልግሎት የሚሰጥበት መሆኑ ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎች ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለሀገራቸው የሚሰጡበት ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በብዝኃነት በደመቁ አገራት ለጋራ እድገትና ብልጽግና የሚያበቃ ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን ገልፀዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጋራ እሴቶች የሆኑትን ርህራሄ እና መተሳሰብን የሚያጎለብቱበት መሆኑን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የማኅበረሰቡን አንገብጋቢ ችግር ለመፍታት እንዲሁም ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል ኃይል መሆኑን ተናግረዋል።

ሥራዎቹን በተደራጀ አግባብ እንዲመራ አስተዋጽዖ እያደረጉ ላሉ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችና በበጎ ፈቃድ ለተሰማሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።


 

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልፀዋል።

ተቋማቱ በቅንጅት መሥራታቸው የኃብት ብክነት እና የሥራ ድግግሞሽ በመቀነስ ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የበጎ ፈቃደኞች የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረው፤ ሥራው በክረምት ብቻ ሳይሆን በበጋውም ጊዜ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።


 

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም የበጎ ፈቃድ ሥራ የህይወት ዘመን የሁልጊዜ ሥራ መሆኑን ገልፀዋል።

ንቅናቄው ጠንካራ አገር ለመገንባት ያለንን ፍላጎት ለማሳካት ርብርብ የምናደርግበት ነው ሲሉ አክለዋል።

ንቅናቄው አብሮነትን በማጠናከር የአገረ-መንግሥት ግንባታ የሚጠናከርበት መሆኑን ጠቁመው፤ በጎነት የሰው ልጅ የሁልጊዜ ተግባር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ተማሪዎች ያለምንም ቀስቃሽ በዚህ መርሃ-ግብር መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአገር ግንባታ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ መርሃ-ግብሩ የእርስ በርስ ትስስርን በማጠናከር አብሮነትን የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥራው በዘመቻ ብቻ ሳይሆን በመደበኛነት የሚከናወንበት አሠራር መገንባት እንደሚገባ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም