ኀብረተሰቡ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያጠናክር መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኀብረተሰቡ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያጠናክር መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ኀብረተሰቡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያጠናክር መገናኛ ብዙሃን ቀጣይነት ያለው ሽፋን በመስጠት አገራዊ ኃላፊነታቸውን ይበልጥ ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ መሰረት የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 'በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ ፅህፈት ቤቱ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር መክሯል።
ምክክሩ የሚያዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ያበረከተው አስተዋጽኦ እና ቀጣይ የድጋፍና ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ነው።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ የግድቡ ግንባታ በዜጎች ያላሰለሰ ጥረትና ርብርብ በመገባደድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት የግድቡ ሁለት ተርባይኖችን ሃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ጠቅሰው አጠቃላይ የግድቡ ግንባታም 96 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የግድቡን ታሪክ፣ የግንባታ ሂደት በመሰነድና በስፋት በማስተዋወቅ እንዲሁም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በግድቡ የግንባታ ሂደት እስካሁን ለነበራቸው የላቀ አስተዋጽኦ አመስግነው፤ የአሁኑ የምክክር መድረክም የባለሙያዎቹን ተሳትፎ ለማጠናከርና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው ብለዋል።
ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ አቶ ታከለ አየለ እንዳሉት፤ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የሚሰሩ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች መገናኛ ብዙሃን በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል።
መገናኛ ብዙሃን ግድቡን በተመለከተ የሰሯቸው ዘገባዎች ተሰንደው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ እንዲሁም ለጥናትና ምርምር ግብዓት መሆን እንዲችሉ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል በበኩላቸው ግድቡን በተመለከተ መገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ መልካም የሚባል ቢሆንም ወጥና ቀጣይነት የሌለው መሆኑ ሌላው ፈተና ነው ብለዋል።
በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ቀጣይነት ያለው ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር፤ለግድቡ ግንባታ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ከኀብረሰቡ ማሰባሰብ ተችሏል ነው ያሉት።
የዳያስፖራ ማህበረሰብን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ርብርብ የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰው የመገናኛ ብዙሃን ድርሻም የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
የህዳሴ ግድብ ሙዚዬም ግንባታን ጨምሮ የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ መገናኛ ብዙኃን የእውቅና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል።