በኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑ ተገለጸ።
የኮሪያ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የፖይ ትርኢት 2024 (2024 K-Pop World Festival,) በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያን የሙዚቃ ስልት በማጣመር በድምጽና በውዝዋዜ የሁለቱ አገራትን ባህል አሳይተዋል።
የባህልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን አንዱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ትኩረት ሲሆን ትርኢቱም ይህንን በተግባር የሚገልጥ እንደሆነ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ፤ ሁለቱ አገራት ታሪካዊ የባህል ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአገራቱን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የሙዚቃና ሌሎች ሁነቶችን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የኮሪያን የሙዚቃ ስልት በውዝዋዜና በድምጽ ማቅረባቸው የሁለቱ አገራት ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይ ቴኳንዶን ጨምሮ የኮሪያ ሪፐብሊክን ባህል ለኢትዮጵያውያን የሚያስተዋውቅ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣትም የባህል ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ1963 የተጀመረ ሲሆን በፖለቲካ፣ በልማት ትብብርና ሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።