በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የስርዓተ ጾታ አካታችነትን ለማሳደግ ሴቶችን በእውቀትና ክህሎት ማብቃት እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የስርዓተ ጾታ አካታችነትን ለማሳደግ ሴቶችን በእውቀትና ክህሎት ማብቃት እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የስርዓተ ጾታ አካታችነትን ለማሳደግ ሴቶችን በእውቀትና ክህሎት ማብቃት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የስርአተ ጾታ እኩልነትና በዘርፉ ለሴቶች ያሉ እድሎች ላይ በአዲስ አበባ አውደ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡
አውደ ጥናቱ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ህንድ ውቅያኖስ የአየር ትራንስፖርት እድገት ውስጥ የጾታ እኩልነት ትኩረት እንዲያገኝ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።
የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ የስርአተ ጾታና ማህበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ቢአትሪስ ሃሙሶንዴ በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ወቅት፤ በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፉ የስርአተ ጾታ አካታችነት መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሁም በአጀንዳ 2063 አቪዬሽን ዘርፉን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስታውሰዋል።
ለዚህም ትብብርን ማጠናከር፣ ቀጣናዊ የስርአተ ጾታ ፖሊሲን ማሻሻል፣ሴቶችና ልጃገረዶችን ዘርፉ የሚጠይቀውን ክህሎት እንዲኖራቸው ከታች ጀምሮ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዘርፉ ተዋናዮች ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው መክረው ኮሜሳ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ከአገራት ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት ጥበቃ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስለሺ ታደሰ ኢትዮጵያ ሴቶችን በማብቃትና የስርአተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን ማከናወኗን ገልጸዋል።
ለዚህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በአብራሪነትና ቴክኒሻን የስራ መስክ ለታዳጊ ሴቶች ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶችን ማፍራት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
ቁጥራቸውን የበለጠ ለማሳደግ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው በሚጠይቀው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግና የትምህርት መስኮች ያላቸውን ብቃት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ መስከረም ገብረሚካኤል ኢትዮጵያ ሴት አውሮፕላን አብራሪዎችን ጨምሮ በአቪዬሽን ዘርፉ ትልቅ ሚና ያላት መሆኗን አንስተዋል።
ባለስልጣኑ አዳዲስ ወደ ዘርፉ የሚመጡ ሴቶች ግንዛቤ ኑሯቸው እንዲገቡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግዋል።
በአውደ ጥናቱ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ ከአየር መንገድ፣ ከግል አቪዬሽን ዘርፍ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
አውደ ጥናቱ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በአቪዬሽን ዘርፉ ለሴቶች ያሉ እድሎችንና የስርአተ ጾታ እኩልነት ላይ ግንዛቤን የሚያሳድጉና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።