ቀጥታ፡

በተለያዩ ምክንያቶች ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የደም መለገስ ልምዳችን ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦በተለያዩ ምክንያቶች ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የደም መለገስ ልምዳችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሰራተኞች በዛሬው ዕለት ለ14ኛ ጊዜ የደም ልገሳ አድርገዋል።


 

ከደም ለጋሾቹ መካከል ጋዜጠኛ የሺመቤት ደመቀ፣ ጋዜጠኛ ሙሴ መለሰ፣ የድምጽ ቅንብር ባለሙያዎቹ ማህሌት ሰለሞንና ኤልሳቤት ቀናው፤ በደማችን አደጋ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት በመታደጋችን ተደስተናል ብለዋል።


 

በተለይም ከወሊድ ጋር በተያያዘ በደም እጥረት ህይወታቸውን ለሚያጡ እናቶችና ህፃናት መድረስ  ትልቅ ሃሴት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ የደም መለገስ ልምዳችን ይቀጥላል ያሉት ጋዜጠኞቹ ደም መለገስ የሁሉም  ዜጋ ባህል ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሃንስ ወንዲራድ፤ "ነገ የምንቀበለውን ደም ዛሬ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መለገስ ይገባል" ብለዋል፡፡

በተቋሙ የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ፤ የኢዜአ አመራርና ሰራተኞች በየሶስት ወሩ ደም በመለገስ ለበጎነት አርዓያ መሆናቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም