ቀጥታ፡

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየት ላይ መሆኑን ገለጸ

 ሮቤ ፤ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን በጥናት በመለየትና መፍትሔዎቹን በማመላከት ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ። 

ዩኒቨርሲቲው በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው። 

በዩኒቨርሲቲው የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ሜጋ የምርምር ፕሮጄክት አስተባባሪ ዶክተር ከድር አብዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በተለይም በደቡብ ምሥራቁ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው። 

በሜጋ የምርምር ፕሮጄክታቸው እስከ አሁን ከ89 የሚበልጡ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶች መለየታቸውን እንደ አብነት አንስተዋል። 

በመዳረሻ አካባቢዎች በጥናት የተለዩ መስህቦቹ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር ከድር፤ለመዳረሻ አካባቢዎቹ የቱሪዝም ልማት ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኘው የአቅም ግንባታ ሥልጠናም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል። 

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር በዛብህ ወንድሙ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ምርምር እያካሄደ ነው። 


 

ዩኒቨርሲቲው በተለይም በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝምና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ላይ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

አክለውም ለአምስት ዓመት የሚቆየውና በቀጠናው የሚገኙ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ኃብቶችን መለየት፣ ማልማትና ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረገው ይኸው ግዙፍ የምርምር ፕሮጄክት የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ ተናግረዋል። 

የምርምር ፕሮጄክቱም በሁለት ዓመት የቆይታ ሂደት በቀጠናው የሚገኙ ዋና ዋና የሚባሉ የመስህብ ሥፍራዎችን የመለየትና በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መሰነድ እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል። 

በመሥህብ ሥፍራዎቹ የተለዩ ተግዳሮቶች በዩኒቨርሲቲውና በሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ ማድረግም የምርምር ፕሮጄክቱ አካል መሆኑን ዶክተር በዛብህ አመልክተዋል። 

ለቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ ባለሙያዎቹ እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠናም በማስጎብኘት ክህሎት፣ በገበያና ብራንዲንግ እንዲሁም በቱሪዝም መዳረሻ አስተዳደር ላይ ያተኮረ እንደሆነ አስረድቷል። 

ከሰልጣኞች መካከል ከሶፍ ዑመር ዋሻ መዳረሻ አካባቢ የመጣው አቶ አብዱልጀባር ሼህ አህመድ በሰጡት አስተያየት የሶፍ ዑመር ዋሻን አልምቶ ለቱሪዝም ልማት ለማዋል በመንግሥት እየተደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል። 

ቅርሱን በማልማትና በማስተዋወቅ ለኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማዋል የሚደረገው ጥረት እንዲሰምርም ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። 

ስልጠናው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለመጎብኘት የሚመጡ ጎብኚዎችን በማስተናገድ ረገድ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ገረመው መብራቱ ናቸው። 


 

ሥልጠናው በተለይም የአስጎብኝ ማህበራት በተለምዶ ሲያካሄዱ የነበሩ ተግባራትን በዕውቀት በመደገፍ የቱሪስት እርካታን በማሻሻል የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እገዛ ያደርጋልም ነው ያሉት። 

በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚገኙ የተፈጥሮ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የድሬ ሼህ ሁሴንና የሶፍ ኡመር ዋሻና ሌሎች በርካታ መስህቦች ይጠቀሳሉ።
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም