በአንድ ጨዋታ 10 ቀይ ካርዶችን የሰጡት "አወዛጋቢው" አርጀንቲናዊ ዳኛ ፋኩንዶ ቴሎ በአውሮፓ ዋንጫ እንዲያጫውቱ እንዴት ተመረጡ ? - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጨዋታ 10 ቀይ ካርዶችን የሰጡት "አወዛጋቢው" አርጀንቲናዊ ዳኛ ፋኩንዶ ቴሎ በአውሮፓ ዋንጫ እንዲያጫውቱ እንዴት ተመረጡ ?
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦ በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።
ዛሬ በምድብ 6 ተርኪዬ ከጆርጂያ ከምሽቱ 1 ሰዓት በሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም የሚጫወቱ ሲሆን፤ ጫዋታውን አርጀንቲናዊ ፋኩንዶ ቴሎ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የዳኞች ኮሚቴ እ.አ.አ ሚያዚያ 23 /2024 በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የሚያጫውቱ 18 ዋና ዳኞችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም 17ቱ ከዛው ከአህጉሩ የተመረጡ ናቸው።
ኮሚቴው ባወጣው የዳኞች ዝርዝር ላይ ከአውሮፓውያኑ ዳኞች ውጪ ከላቲን አሜሪካ አርጀንቲናዊውን የ42 ዓመት ዳኛ ፋኩንዶ ቴሎ ከሁለት ረዳቶቻቸው ጋር እንደሚያጫውቱ አስታውቋል።
ውሳኔው በአውሮፓ መድረክ የሌላ አህጉር የመጣ ዳኛ ለምን በውድድሩ ላይ እንዲያጫውት ተመረጠ? የሚል ጥያቄ መጫሩ አይቀርም።
ነገሩ እንዲህ ነው:-
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) እና የደቡብ አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CONMEBOL) እ.አ.አ የካቲት 12 ቀን 2020 በአህጉራቱ የስፖርት ልማት እድገት ተቀራርቦ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ሰነዱ እ.አ.አ ታህሳስ 15 ቀን 2021 የትብብር አድማስን በሚያሰፋ መልኩ ማሻሻያ ተደርጎበት ሁለቱ አህጉራዊ የእግር ኳስ ተቋማት ሁለተኛ ስምምነት ተፈራረሙ።
እ.አ.አ ጥር ወር 2022 የዩኤፋ እና ኮንሜቦል ባለስልጣናት በፓራጓይ አሱንሲዮን ባደረጉት ስብስባ ስምምነቱን አጽድቀውታል።
የትብብር ስምምነቱ ሁለቱ ወገኖች በጋራ የሚያዘጋጁት አዲስ የውድድር አይነትን መፍጠር የሚፈቅድና ተቋማቱ በሚያዘጋጇቸው አህጉራዊ ውድድሮች የዳኞች ልውውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው።
አርጀንቲናዊው ፋኩንዶ ቴሎ በአውሮፓ ዋንጫ እንዲያጫውቱ መመረጥ የዚህ የትብብር ስምምነት አካል መሆኑን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አስታውቋል።
ፋኩንዶ ራውል ቴሎ ፊገሮዋ እ.አ.አ ግንቦት 4 1984 በአርጀንቲና ቦነስአይረስ ግዛት በምትገኘው ባሂያ ብላንካ ተወለዱ።
ቴሎ የዳኝነት ጉዟቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ2011 በአርጀንቲና ሁለተኛ ዲዚዮን በማጫወት ሲሆን 4 ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት መርተዋል።
አርጀንቲናዊው ዳኛ እ.አ.አ በ2013 በአርጀንቲና የመጀመሪያ ዲቪዚዮን ማጫወት የጀመሩ ሲሆን በዋና ዳኝነት የመሩት የመጀመሪያ ጨዋታ በጎዶይ ግሩዝና ቬሌዝ ሳርስፊልድ መካከል የተደረገውን ጨዋታ ነው።
በአርጀንቲና በሚካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ላይ በማጫወት የቀጠሉት ቴሎ እ.አ.አ 2019 የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ዓለም አቀፍ ዳኛ ዝርዝር ውስጥ አካተታቸው።
እ.አ.አ በ2022 በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ካጫወቱ ዋና ዳኞች መካከል አንዱ ናቸው ቴሎ።
የ42 ዓመቱ ጎልማሳ እ.አ.አ ሕዳር 6 2022 በአርጀንቲና ሻምፒዮንስ ትሮፊ የፍጻሜ ጨዋታ የዓለምን ትኩረት እንዲያርፍባቸው አድርጓል።
ቦካ ጁኒየርስና ሬሲንግ ክለብ ባደረጉት ጨዋታ ፋኩንዶ ቴሎ 10 ቀይ ካርዶችን በመምዘዝ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ጉድ አሰኝተዋል።
እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ዊሊያም ጊቲንስ በስፔኑ ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ ማርካ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ የቴሎን “ታይቶ የማይታወቅ” ውሳኔ ሲል ገልጾታል፡፡
ቦካ ጂነየርስና ሬሲንግ ክለብ በመደበኛው 90 ደቂቃ አንድ አቻ ተለያይተው ጨዋታው ወደ ጭማሬ ሰዓት አመራ።
የ30 ደቂቃ ጭማሬ ማብቂያ ደቂቃዎች ላይ የአማካይ ተጫዋቹ ካርሎስ አልካራዝ ሬሲንግ ክለብን አሸናፊ ያደረገችውን ግብ አስቆጠረ።
አልካራዝ ደስታውን የቦካ ጁኒየርስ ደጋፊዎች ባሉበት ቦታ የገለጸ ሲሆን ይህም የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎችን ማስቆጣቱን ፀሐፊው ይገልጻል።
የቦካ ደጋፊዎች የአልካራዝን ጆሮ በመያዝና የመጫዋቻ ኳስ ፊቱ ላይ ወረወሩበት። ይህም በሜዳው ድብድብ እንዲነሳ መንስኤ ሆነ።
ፋኩንዶ ቴሎ ለፀቡ መነሻ ምክንያት ነው ያሉትን ካርሎስ አልካራዝን በቀይ ካርድ ከሜዳ ያሰናበቱ ሲሆን ሌሎች 5 የቦካ ጁኒየርስ ተጫዋቾችን ስፖርታዊ ስነ ምግባርን በመጣስ በግርግሩ ተሳትፈዋል ያሏቸውን ተጫዋቾች ላይም ቀይ ካርድ መዘዋል።
ቴሎ ከተፈጠረው ክስተት በፊት 3 የሬሲንግ ክለብ ተጫዋቾችንና ከቦካ ጂነየርስ ሁጎ ኢባራን በቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተዋል።
እንደ ጊቲንስ ገለጻ፤ አርጀንቲናዊው ዳኛ ለቦካ ጁነየርስ ተጫዋቾች 7 እንዲሁም ለሬሲንክ ክለብ ተጫዋቾች 3 በድምሩ 10 ቀይ ካርድ ሰጥተዋል።
ካርድ ከደረት ኪሳቸው ለመመዘዝ ቅርብ ናቸው የሚባሉት ፋኩንዶ ቴሎ በጨዋታው የመዘዟቸው ቀይ ካርዶች መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።
ፋኩንዶ ቴሎ በአውሮፓ ዋንጫ በሚኖራቸው ተሳትፎ ጥፋቶች በተፈጸሙ ቁጥር ቢጫና ቀይ ካርዶችን በፍጥነት መምዘዛቸውን ይቀጥላሉ? ወይስ የትዕግስት መጠናቸውንና ገደባቸውን ጨምረው ያጫውታሉ? የእግር ኳስ ቤተሰቡ ጥያቄዎች ናቸው።