ቀጥታ፡

የጨረር ህክምና የሚሰጡ ማዕከላትን በማስፋት የካንሰር ህክምና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው -ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦የጨረር ህክምና የሚሰጡ ማዕከላትን በማስፋት የካንሰር ህክምና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

ማህበሩ ከተቋቋመ 20 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ፤ ህብረተሰቡ ለካንሰር ተጋላጭ ከሚያደርጉ ነገሮች ራሱን እንዲጠብቅ እና ቅድመ ምርመራ የማድረግ ልምዱን እንዲያዳብር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ በሰፋት ይሳተፋል፡፡

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴርን ወክለው ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን፤በኢትዮጵያ የጨረር ህክምናን ማስፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የካንሰር ህክምናን በብቸኝነት እየሰጠ ያለው የጥቁር አንበሳ ስፒሻላይዝድ ሆስፒታል እንደነበር ገልጸው አሁን በጅማ፣ሐሮማያ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች እንዲሁም በመቀሌ አይደር ሆስፒታል አገልግሎቱ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጨረር ህክምና የሚሰጡ ማዕከላትን ወደ ሰባት ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከልም ከ6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ልጃገረዶች የክትባት አገልግሎት መሰጠቱንና ቅድመ ምርመራ አገልግሎትን በጤና ጣቢያዎች ጭምር ማስጀመር መቻሉን  አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተልና ከጎጂ ሱሶች በመራቅ ራሱን መጠበቅ እንዳለበትም መክረዋል፡፡ 

ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች ላይ የላቀ አስተዋጾ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና ሰርተፍኬት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም