ቀጥታ፡

ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፈራረም በአቪዬሽን ዘርፍ በስፋት ሥልጠና ለመስጠት እየሰራን ነው - የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፈራረም በአቪዬሽን ዘርፍ በስፋት ሥልጠና ለመስጠት እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሥር ካሉ ተቋማት መካከል የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተቋቁሞ ብቃት ያላቸው የዘርፉ ሙያተኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ መስተንግዶ፣ በኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በንግድና ሽያጭ ዘርፍ ሥልጠና ይሰጣል፡፡

በዚህም ከኢትዮጵያ ባለፈ በአህጉሪቱ ብቁ ሙያተኞችን ማፍራት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ነው ያብራሩት፡፡

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም የሰው ኃይል በብዛት እንድናሰለጥንላቸው ከተቋማችን ጋር የመግባቢያ ስምምነት እየተፈራረሙ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት በመምጣት የአቪዬሽን ሥልጠና ይወስዱ የነበሩ የዘርፉ ሙያተኞች መኖራቸውን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በሀገራት ደረጃ የመግባቢያ ስምምነት እየተደረገ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ከተቋሙ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ ሀገራት መካከል ኒጀር እና ጋቦንን ለአብነት አንስተው፤ ከሌሎች ሀገራት ጋርም መሰል ስምምነት ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ ካሉ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህንኑ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ የኤሮ ስፔስ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የጀመረው ሥራም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መከተል የሚፈልግ መሆኑን በመጥቀስ፤ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ ዘመኑ ያፈራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን አቪዬሽን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያውያን ባለፈ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የአፍሪካ ሀገራት ዜጎችን ማሰልጠን የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በበጀት ዓመቱ ሲያሰለጥናቸው ከቆዩት ሙያተኞች መካከል በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በአውሮፕላን ጥገና እና ሌሎች ዘርፎች በሦስት ዙር ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 965 ሙያተኞች ማስመረቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም