ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናውና ለአፍሪካ ሠላም ቀጣይነት ባለው መልኩ እየሰራች ነው - ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለቀጣናውና ለአፍሪካ ሠላም ቀጣይነት ባለው መልኩ ስትሠራ የቆየችና አሁንም ብዙ ዋጋ እየከፈለች ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ።

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑካን ቡድን በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ በተጀመረው የብሪክስና አጋር አገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።


 

የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) "undivided and equal security as a key principle for building genuine and lasting international peace" በሚል የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት ፓርቲያቸውን በመወከል ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለቀጣናውና ለአፍሪካ ሠላም ቀጣይነት ባለው መልኩ ስትሠራ የቆየችና አሁንም ብዙ ዋጋ እየከፈለች መሆኑን በማውሳት ለዚህ ማሳያነት የፀጥታ ችግር በገጠማቸው የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያ ከጎናቸው ነበረች ብለዋል።

የሩሲያ መንግስት በማንኛውም አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳየው አጋርነት ያመሰገኑት ዶክተር ሰማ ይኸው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የብሪክስ መድረክ ሀገራትም ለሠላማቸው በጋራ የሚተባበሩበት እንዲሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በተለይም ለሠላም ጠንቅ የሆነውን ድህነትና ኋላቀርነት ለማስወገድ የብልፅግና ፓርቲ በትኩረት እየሠራና አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የብሪክስ አባል ሀገራት በትብብርና በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም