የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ርብርብ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ መሰረት የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 'በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ ፅህፈት ቤቱ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር እየመከረ ነው።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ የግድቡ ግንባታ በዜጎች ያላሰለሰ ጥረትና ርብርብ በመገባደድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት መጀመራቸውን ጠቅሰው አጠቃላይ የግድቡ ግንባታም 96 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የግድቡን ታሪክ፣ የግንባታ ሂደት በመሰነድና በስፋት በማስተዋወቅ እንዲሁም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።
በግድቡ የግንባታ ሂደት እስካሁን ለነበራቸው የላቀ አስተዋጽኦ አመስግነው የአሁኑ የምክክር መድረክም የባለሙያዎቹን ተሳትፎ ለማጠናከርና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው ብለዋል።