ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን በበቂ ሁኔታ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባህሪ መገንዘብ ወሳኝ ነው - አቶ አዲሱ አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን በበቂ ሁኔታ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባህሪ መገንዘብ ወሳኝ ነው - አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦ በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለውን ሃሰተኛ መረጃ በበቂ ሁኔታ ለመታገል የወቅቱን የሚዲያ ባህሪ በአግባቡ መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሔደውና ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።
“ኃላፊነት የተሞላበት የመረጃ ስርጭት ፍትሐዊ የዓለም ስርዓትን ከመገንባት አንጻር” በሚል ርዕስ በተስተናገደው የፎረሙ ክፍል ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ አዲሱ በአሁኑ ወቅት ያልተረጋገጠ የተዛባና ሃሰተኛ መረጃ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በፍጥነት የሚሰራጭበት ሁኔታ እየታየ ነው ብለዋል።
የዚህ ዓይነቱን ችግር ለመቋቋም ቴክኒካዊ መፍትሔ ብቻ ሳይሆን ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ የሚዲያ ባህርያት የመረዳት ባህል ሊዳብር እንደሚገባም አስረድተዋል።
በዚህም ለእውነት፣ ለትክክለኛነት፣ ለታማኝነትና ለግልጽነት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
አቶ አዲሱ እነዚህን የድህረ እውነት ዓለም ፈተናዎች ለመቋቋም ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል ሕዝቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን ትክክለኛነትና የመረጃ ምንጩን ተቀባይነት እንዲያጣራ ማስተማር ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል።
ሃሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ባከበረ መልኩም ሃሰተኛ የመረጃ ስርጭቶችን መከላከል የሚያስችል የተጠያቂነት የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ የማድረግን አስፈለጊነትም አንስተዋል ።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስትና መረጃን በማጣራት በተሰማሩ አካላት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር የሃሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ተከታትሎ ማጋለጥ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ፖሊሲ የዜጎችን ብዝሃነት ታሳቢ ያደረገ ሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለና የወዲፊቷን ዲጂታል ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
የተሻሉ ተሞክሮዎችንና ፈጠራዎችን በማጋራት፣ እድገትን፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን የሚያበረታታ ጠንካራ ዲጂታል አካባቢ መፍጠር እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር በጋራ በመስራት የዲጂታላይዜሽንን የለውጥ አቅም ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት አቶ አዲሱ በጋራ ፍትሃዊ ፣ አካታችና ስኬታማ አለምን እንገንባ ማለታቸውን ኢዜአ ከስፍራው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በፎረሙ ላይ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ በብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ እየተሳተፉ ይገኛሉ።