ከተረጂነት ለመውጣት ዜጎች ዋነኛ የልማት አቅም መሆናቸውን በማስገንዘብ የልማትና የለውጥ ቁጭት እንዲፈጠር እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከተረጂነት ለመውጣት ዜጎች ዋነኛ የልማት አቅም መሆናቸውን በማስገንዘብ የልማትና የለውጥ ቁጭት እንዲፈጠር እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016(ኢዜአ)፦ ከተረጂነት ለመውጣት ዜጎች ዋነኛ የልማት አቅም መሆናቸውን በማስገንዘብ ከፍተኛ የልማትና የለውጥ ቁጭት እንዲፈጠር እየተደረገ መሆኑን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
መንግሥት ለብዝኃ ኢኮኖሚ ግንባታ የሰጠው ትኩረት ዕድሎችን በመጠቀም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በአገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን፣ ተረጂነትና ሕዝባዊ የምክክር መድረኮችን፣ የገበያ ትስስር፣ የወጪ ንግድና ተያያዥ ጉዳዮችን በስፋት አንስተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ በለውጡ ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ስብራትን መጠገን ያስቻሉ ስኬታማ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትከተለው የነበረውን ጠባብ የኢኮኖሚ ዕይታ ማዕቀፍ በመቀየር ለብዝኃ ኢኮኖሚ ግንባታ የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱንም ገልፀዋል።
በዚህም በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና በአይ.ሲ.ቲ. የኢኮኖሚ መሰሶዎች በብዝኃ ኢኮኖሚ ግንባታ ተጨባጭ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 800 የአሜሪካ ዶላር እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በእጥፍ ማደጉን ተናግረዋል።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን የምጣኔ ኃብት እድገት በውጤት የታጀበ፣ ቀጣይነት ያለውና ዓለም አቀፍ ዕውቅናም የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች የጠገነና ከመሰረቱ የቀየረ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ሀገራዊ ዕምቅ የመልማት አቅም ከዜጎች የተጠቃሚነት ፍላጎት ጋር ማገናኘት ያስቻለ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከተረጂነት ለመውጣት ዜጎች ዋነኛ የልማት አቅም መሆናቸውን በማስገንዘብ ከፍተኛ የልማትና የለውጥ ቁጭት እንዲፈጠር እየተደረገ መሆኑንም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አብራርተዋል።
በተለያዩ ከተሞች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ አገራዊ ክብር እና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ሕዝባዊ መድረክ በኢኮኖሚው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ከተረጂነት መውጣት እንደሚቻል ምስክርነት እንደተቸራቸው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያውያን አቅማቸውን በመጠቀም የለውጥ ምሳሌ ሆነው ማየት የኢትዮጵያ ራዕይ በመሆኑ በቤተሰብ ደረጃ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ በመፍጠር ጥራት ያለው አገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተረጂነት ላይ ያለውን ጎጂ እሳቤ በማስቀረት ዜጎች እራሳቸውን ችለው ለሌሎች የሚተርፉበት አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የግብይት ሰንሰለት መሠረተ-ልማትና የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የአምራችና ሸማችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።
በጅምላና ችርቻሮ ወጪና ገቢ ምርት ንግድ ለውድድር ክፍት መደረጉ ግብይትን በማነቃቃት የአገርን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ለዚህም የአገር ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግ ጤናማ የግብይት ሥርዓት በመፍጠር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት "ስታርት አፖች" ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው በመገንዘብ ለወጣቶች ፈጠራና ክህሎት መጎልበት ልዩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በዚህም ስታርት አፖች በውጭ ምንዛሬ፣ በንግድ፣ ጉምሩክና ፋይናንስ ዘርፍ ለሚያጋጥማቸው ችግር መፍትሔ በመስጠት ዋነኛ የልማት አቅም እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን መንግሥት ተረጂነትን ለማስቀረት የጀመረውን ስኬታማ የልማትና የመሪነት ሚና በማገዝ በከፍተኛ ቁጭትና የታታሪነት መንፈስ መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።