ቀጥታ፡

ግብረ ሀይሉ በፌደራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን የአፈጻጸም ሂደት ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር ገመገመ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 11/2016 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በክልሉ ርዕሰ መሰተዳደር የተቋቋመው ግብረ ኃይል የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ሂደት ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር ገመገመ።

በክልል ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የአስፋልት መንገዱን የስራ እንቅስቃሴ፣ የጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል እየተሰራ ያለውን ሂደትና የመገጭ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ገምግሟል።

የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሴ አሰሜ እንደገለፁት በጎንደር ከተማ በፌደራል መንግስት እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ ነው።

የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በአጭርና በረዥም ጊዜ በእቀድ በተያዘው መሰረት በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶችን በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት ትኩረት የሚሽ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የመገጭ ግድብ አዲሱ ተቋራጭ በክርምቱ አጠቃላይ የቅደም ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በየዘርፉ የሚሰሩ ቢሮዎች ከፌዴራል መንግስት ጋር እየተገኛኙ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ደሴ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ በበኩላቸው በፌደራል መንግስት እየተገነቡ ያሉ 3ቱ ፕሮጀክቶችን በፌደራል፣ በክልልና በአካባቢው መስተዳድር ተቋማት ተቀናጅቶ በመሰራት በፍጥነት ተከናውነው ለህዝብ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አዘዞ -አርበኞች አደባባይ የአስፓልት መንገድ ስራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የተቋራጩ ውል ተሰርዞ ለኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ካዘው በኃላ የአስፓልት መንገድ ሰራ በተሻለ ደረጃ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከስትራክቸር ስራው ጎን በጎን የአስፓልት ንጣፍ ስራው ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን ዶክተር ጋሻው ገልጸዋል።

የመገጭ ግድብ ለአዲስ ተቋራጭ ውል የተሰጠ ሲሆን 1ዓመት ከ6ወራት ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብ እንደተሰጠው መገለጹ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላከታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም