ቀጥታ፡

ፈረንሳይ በአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋ ድል ቀናት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በምድብ 5 ሁለተኛ ጨዋታ ፈረንሳይ ኦስትሪያን 1 ለ ዐ አሸንፋለች።

በዱሲልዶርፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ በ38ኛው ደቂቃ የፈረንሳይ አምበል ኪሊያን ምባፔ በቀኝ ክንፍ ያሻገረውን ኳስ የኦስትሪያው ተከላካይ ማክሲሚሊያን ዎበር በራሱ መረብ ላይ ያሳረፈው ግብ ሰማያዊዎቹን አሸናፊ አድርጓል።

ምባፔ በ55ኛው ደቂቃ ከኦስትሪያው ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ፔንትዝ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የሳተው ኳስ የሚያስቆጭ እድል ነበር።

የ33 ዓመቱ አጥቂ አንቶዋን ግሪዝማንም ግልጽ የግብ እድል አግኝቶ አልተጠቀመበትም።

ትናንት በምድብ 5 በተካሄደው የመጀመሪያ ጨዋታ ኔዘርላንድ ፖላንድን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

በምድብ 4 ቀጣይ መርሐ ግብር ኔዘርላንድ ከፈረንሳይ፣ ፖላንድ ከኦስትሪያ ይጫወታሉ።

የማክሲሚሊያን ዎበር ጎል በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በራስ ላይ የተቆጠረ ሁለተኛ ግብ ሆኗል።

ጀርመንና ስኮትላንድ ባደረጉት የውድድሩ መክፈቻ ጨዋታ የጀርመኑ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር በራሱ ግብ ላይ ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።

ዛሬ በምድብ 5 በተደረጉ ጨዋታዎች ሮማኒያ ዩክሬንን 3 ለ 0 ስትረታ ስሎቫኪያ ሳትጠበቅ ቤልጂየምን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል በምድብ 6 ጆርጂያ ከተርኪዬ ከምሽቱ 1 ሰዓት ፣ ፖርቹጋል ከቼክ ሪፐብሊክ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም