ቀጥታ፡

 በካሜሮን ለሚደረገው በ23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚካፈለው ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ሽኝት ተደረገለት  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016 (ኢዜአ)፦ በካሜሮን ዱዋላ ለሚደረገው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሚካፈለው ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት ሽኝት ተደረገለት። 

23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከተዘጋጁት 45 የሜዳ ላይ ተግባራት በ41ዱ ትሳተፋለች።

በሴት 34፣ በወንድ ደግሞ 43 አትሌቶችን በድምሩ 77 አትሌቶችን ትሳትፋለች።

ልዑካን ቡድን ከነገ በስትያ ረቡዕ ጠዋት 3 ሰዓት ላይ ወደ ካሜሮን ዱዋላ እንደሚጓዝ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


 

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በሽኝት መርሃ ግብሩ፤ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንደ ኦሊምፒክ ላሉት ውድድሮች መነሻ ነው ብለዋል። 

ይሄ ዓመት ውድድሮች የበዙበት ፈታኝ ዓመት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብቁ አትሌቶቹን ለማብቃት ያደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባል ነው ያሉት።  

የእያንዳንዱ አትሌት ምኞት ውጤት ማምጣትና ኦሊምፒክ መሳተፍ በመሆኑ እንደ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያሉት ውድድሮች ትልቅ መነሻ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 


 

ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ፤ አትሌቶች በቆዩበት የ15 ቀናት የልምምድ ጊዜ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ረድቷቸዋል ብላለች። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም