ቀጥታ፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በጂንካ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ጂንካ፤ ሰኔ 10/2016 (ኢዜአ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በጂንካ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

ላለፉት 15 ቀናት የተካሄደው ውድድር የተጠናቀቀው ዛሬ ማምሻውን ነው።

በውድድሩ 17 ክለቦች መሳተፋቸውን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አኩዬ ጌካ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሻምፒዮና ውደድሩን ያዘጋጀው የጂንካ ከተማ አስተዳደር መሆኑን ጠቁመው፤ በውድድሩ ጂንካ፣ ሳላማጎ፣ ባስኬት ቡና እና ብርብር ሞሌ ክለቦች ለግማሽ ፍፃሜው መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

ዛሬ በጂንካ ሁለገብ ስታድየም የተካሄደው የዋንጫ ጨዋታ ጂንካ ከተማ እና ባስኬት ቡና መደበኛውን የውድድር ሰዓት 1 ለ 1 አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።

በመጨረሻም በተሰጠው የመለያ ምት የጂንካ እግር ኳስ ክለብ ተጋጣሚውን 3 ለ 0 ረቶ የዋንጫው አሸናፊ ሆኗል።

የአርባ ምንጭ "ብርብር ሞሌ እግር ኳስ ክለብ" በውድድሩ የ3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። 

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ 3ኛ የወጡ ክለቦች በቀጣይ በድሬዳዋ በሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ክልሉን ወክለው እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ከግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ይሄ ውድድርም ክለቦቹን ለመለያት የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም