ቀጥታ፡

ተ.መ.ድ ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016 (ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ገለጹ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል። 

ውይይቱ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ገልጸዋል። 

በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ተናግረዋል። 

ጎን ለጎንም በቀጣይ መስከረም በሚካሄደው የተመድ ''የመጪው ዘመን ጉባዔ' እና የፊታችን ሐምሌ በኢትዮጵያ በሚካሄደው ''የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ'' ዙሪያ መምከራቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሬዝዳንት ፍራንሲስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት ማድነቃቸውን ቃል አቀባዩ አንስተዋል።

መንግሥት ውስጣዊ ግጭቶች በሰላም እንዲፈታ ያለውን ቁርጠኛ አቋም አድናቆት እንደቸሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለምታካሂዳቸው የልማት እንቅስቃሴዎችና ለሰላም ማስፈን ሂደቶችን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ እንዳረጋገጡ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥና በቀጣይነት በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ በትኩረት እንደምትሰራ ለፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት ሪፎርም በተለይም አፍሪካና ታዳጊ አገራት በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራቸው የሚል ኃሳብ ማንሳታቸውን እንዲሁ።

ፕሬዝዳንት ፍራንሲስ በኃላፊነት ዘመናቸው የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የታዳጊ አገራት አጀንዳዎች በሆኑ ጉዳዮች በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በአቅም ግንባታና በዘላቂ ልማት ግቦች ድጋፍ እንዲደረግ ለተጫወቱት ሚና ማመስገናቸውንም ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም