ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደረሰ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በ2016 ዓ.ም ብቻ ከሶስት መቶ በላይ ዝርፊያዎች የተፈጸሙ ሲሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በተቋሙ ሃብት ላይ ኪሳራ መድረሱ ተገልጿል።

በተቋሙ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ሲዘረፉ በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በቅርቡም ህገ-ወጦች የተቋሙ ሰራተኞች ነን ቆጣሪ እናስገባ በሚል ከስምንት ደንበኞች ከ30 እስከ 40ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከተለያዩ አካባቢዎች ሲቀበሉ የነበሩ ህገ-ወጦች  በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ የ18 ዓመት ጽኑ እስራትና የ20 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል ብለዋል።

በተመሳሳይ በህገ ወጥ መንገድ ቆጣሪ ለማስገባትና ያልተገባ ጥቅም በመጠየቅ ተሳትፈው የተገኙ ሶስት የተቋሙ ሰራተኞች ተቋሙ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል። 

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተፈጸሙ ከሶስት መቶ በላይ  ወንጀሎች ውስጥ  በ31 ግለሰቦች ላይ ብቻ ከአንድ ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ይህም ወንጀል ፈጻሚዎችን ተከታትሎ ተገቢውን ፍርድ መስጠት ላይ ያለው ውስንነት የወንጀል ፈጻሚዎቹ ቁጥር እንዲበራከት እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በቀጣይም ስርቆት በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ተለይተው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ የአንድ ተቋም ሃላፊነት ብቻ አለመሆኑን ተረድተው፤ ወንጀልን በመከላከል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮ ቴሌኮምና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ሁሉም ሰው እንዲጠብቅ የሚያስገደድ አዋጅ  1997/464 መውጣቱ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም