በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት አገልግሎት መስጠት የተከለከሉ የ41 ትምህርት ተቋማት ዝርዝር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በ2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት አገልግሎት መስጠት የተከለከሉ የትምህርት ተቋማትን ዝርዝር ይፋ አደረገ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን መዝግበው የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 332 መሆናቸውንና የማስተማር ፈቃድ የተሰጣቸው እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

41 ትምህርት ቤቶች በዋናነት በትምህርት ፖሊሲ ጥሰት ፣ በትምህርት ስታንዳርዱ መሰረት ከ 75% በታች ያመጡ እንዲሁም የትምህርት ጊዜ ሰሌዳን በአግባቡ አለመጠቀም ችግር የታየባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በልጆች አስተዳደግ ላይ ተፅእኖ የሚፈጥርና ብቁ ትውልድ በማፍራት ሒደቶች ላይ እንቅፋት የሚፈጥር በመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ ባለስልጣኑ ውሳኔ ላይ መድረሱን ዋና ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል::

መስፈርቱን ባለማሟላታቸው በተዘጉ ትምህርት ቤቶች ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያለምንም ዋጋና መሰል ልዩነቶች ምርጫቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

43 ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ጊዜ መቀጠል ስላልቻሉ ፈቃዳቸው መሰረዙንም ዋና ስራ አስኪያጁ መግለጻቸውን ከከተማው ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም