ቀጥታ፡

የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ስራ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ

ጎንደር ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦ የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ስራ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በክልሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሂደትን የሚከታተለው ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

በክልል ደረጃ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የአስፋልት መንገዱን የስራ እንቅስቃሴ በአካል በመገኘት ዛሬ ምልከታ አካሄዷል፡፡


 

ግብረ ኃይሉን የወከሉት የክልሉ መንገድ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ሥራውን በባለቤትነት እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች ናቸው፡፡


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሰጠው አመራር ዳግም በፍጥነት እንዲጀመር በተደረገው የመንገድ ሥራ እስካሁን የአንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ስራ ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

እስከ ሰኔ መጨረሻ በአጠቃላይ ሶስት ኪሎ ሜትር አስፋልት ለማንጠፍ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ዕቅዱን ለማሳካትም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው ተቋራጭ የመንገድ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ አስከትሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከአስፋልት ማንጠፍ ስራው ጎን ለጎን እየተከናወኑ ያሉ የድጋፍ ግንብ ስራን ጨምሮ የመንገድ አካፋይ ስራዎች በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ግብረ ኃይሉ በምልከታው ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በፍጥነትና በጥራት ተገንብቶ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ለማድረግም የፌደራል የክልልና የጎንደር ከተማ አስተዳደር በጋራና በተናጠል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት እንደሚገኙም አብራርተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መንገዱ ከሶስተኛ ወገን ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆን ማድረግ ችሏል ያሉት የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ናቸው፡፡ 


 

የመንገድ ፕሮጀክቱ መጓተትና መዘግየት በከተማው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አመራር አሁን የመንገዱ ግንባታ ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

በምልከታው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሴ አሰሜን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

12 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ስራ በ2009 ዓ/ም የተጀመረ መሆኑን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም