ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ በተለያዩ የትብብር መስኮች ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት በፖለቲካ፣ በምጣኔ ኃብትና በልማት ዘርፎች ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በሌሎች የትብብር ዘርፎችም እየሰፋ መምጣቱንም ነው ያነሱት።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪያ ሪፐብሊክ የነበራቸው ጉብኝትም እያደገ የመጣውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
በይፋዊ የሥራ ጉብኝቱ ወቅት፤ ሁለቱ አገራት በኢትዮጵያ ፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንና በደቡብ ኮሪያ ፀረ-ሙስናና ሲቪል መብቶች ኮሚሽን መካከል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በቀጣይ አራት ዓመታት ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች የ1 ቢሊየን ዶላር የፋይናንስ ማዕቀፍ ሥምምነትም ተፈራርመዋል፤ ይህም ሥምምነት የሀገራቱን ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተለይም ሁለቱ ሀገራት የደረሱት የፋይናንስ ትብብር የድጋፍ ሥምምነት ኢትዮጵያ የተሻለ ምጣኔ ኃብትን በመገንባት ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እያከናወነች ላለው ተግባር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለሥምምነቶች ተግባራዊነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በባህልና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በትኩረት በመሥራት የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የልማት ትብብር የሁለቱ ሀገራት ዋነኛ የአጋርነት መስክ ሆኖ እንደሚቀጥል የገለጹት አምባሳደሩ መሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ኃይል፣ ትምህርና ሌሎችም የትኩረት መስኮች የዚህ የትብብር አካል መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1963 መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ።