ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወቅታዊ የአየር ጠባይና ሁኔታ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወቅታዊ የአየር ጠባይና ሁኔታ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ወቅታዊ የአየር ጠባይና ሁኔታ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአየር ጠባይና ሁኔታ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ለዜጎችና ለተቋማት በወቅቱ ተደራሽ እየተደረገ ነው።
የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት አደጋን በመቀነስ የበጋ፣ የበልግና በመኸር ወቅቶች ውጤታማ የግብርና ሥራዎችን እንዲከውኑ ጥራት ያለው የተተነተነ የአየር ጠባይ መረጃ እንዲደርሳቸው እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋትና ብቁ የሰው ኃይል በመገንባት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የአየር ጠባይና ሁኔታ ትንበያ አገልግሎት በመስጠት የአገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማሳለጥ እገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ 1 ሺህ 301 የገፀ-ምድር የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችና 300 የሚሆኑ ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎች እንዲሁም ሦስት የከፍታ አየር መመዝገቢያ ጣቢያዎች መተከላቸውን ተናግረዋል።
የአየር ሁኔታና ጠባይ መሰረተ-ልማቶችን ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የሚከሰቱ የአየር ብክለት ሁኔታ ጠቋሚ ዘመናዊ የራዳር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ለመትከል እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጣቢያዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የሚተከሉ መሆኑን ጠቅሰው 250 ኪሎ ሜትር ራዲስ ውስጥ መረጃዎችን በፈጥነት ለመሰብሰብ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
የአየር ጠባይና ሁኔታ አመላካች የትንበያ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን ለቅድመ ማስጠንቀቂያና ልማት ሥራ እገዛ እንዲኖራቸው ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የአየር ጠባይ ክስተቶችን ከግምት በማስገባት የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለድርሻ አካላት የሚሰጠውን የአየር ሁኔታና ጠባይ መረጃን በመጠቀም አደጋን በመቀነስና መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።