አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ጋር ተወያዩ።
አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴና ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮችና በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ዙሪያ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የታዳጊ ሀገራት አጀንዳዎች በሆኑ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ የአቅም ግንባታ ድጋፎች እንዲሁም በዘላቂ ልማት ግቦች ማረጋገጥ ጉዳዮችም እንደተወያዩ አንስተዋል።
አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ኢትዮጵያ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የምትሰጠውን ትልቅ ቦታ እንዲሁም በቀጣይ በሚካሄደው 'summit of future' የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተመለከተም ዝርዝር ውይይት ስለማድረጋቸው ጠቅሰዋል።
አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ በሚደረግ ጥረትና መሰል የፀጥታ ጉዳዮችም የውይይቱ አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በቀጣናው የሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት ማድነቃቸውን ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
መንግስት ውስጣዊ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ማድነቃቸውንም እንዲሁ።
ለልማት እንቅስቃሴዎችም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ስለመሆኑም አንስተዋል።