ቀጥታ፡

የአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች

እ.አ.አ ሐምሌ 6 ቀን 1960፤ የመጀመሪያው የአውሮፓ ዋንጫ (በቀድሞ አጠራሩ ኢሮፒያን ኔሽንስ ካፕ) የተጀመረበት ቀን ነው።

ይህን የመጀመሪያ ታሪካዊ ውድድር ያዘጋጀችው ፈረንሳይ ስትሆን የያኔዎቹ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ሶቪየት ሕብረትና ዩጎዝላቪያ በውድድሩ ላይ የተሳተፉ አገራት ናቸው።

የውድድሩ ተሳታፊ አገራት 4 በመሆናቸው ጨዋታዎች የጀመሩት ከግማሽ ፍጻሜ መርኃ ግብር ነው።

የመጀመሪያውን የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ ያደረጉት አዘጋጅ አገር ፈረንሳይና ዩጎዝላቪያ ሲሆኑ ዩጎዝላቪያ በፓርክ ዴ ፕሪንስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ 5 ለ 4 በማሸነፍ ወደ ፍጻሜው አለፈች።

የዩጎዝላቪያው አጥቂ ሚላን ጋሊች የውድድሩን የመጀመሪያ ግብ በማስቆጠር ታሪክ ሰራ።

በፍጻሜው ጨዋታ ሶቪየት ሕብረት ዩጎዝላቪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ታሪካዊውን የመጀመሪያ ዋንጫ አነሳች።

ፈረንሳያዊው ፍራንስዋ ሁት፣ የሶቪየት ሕብረቶቹ ቫለንቲን ኢቫኖቭና ቪክቶር ፖንዴልኒክ እንዲሁም የዩጎዝላቪያዎቹ ሚላን ጋሊችና ድራዛን ጄርኮቪች በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በጋራ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን አጠናቀቁ።

የመጀመሪያው የአውሮፓ ዋንጫ ከተካሄደ 64 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በነዚህ ጊዜያት ታላላቅ ግብ አስቆጣሪዎችን በውድድሮቹ ላይ መመልከት ተችሏል ።

ከቀደምቶቹ ፈረንሳያዊው ሚሼል ፕላቲኒ፣ ጀርመናውያኑ ኮከቦች ገርድ ሙለርና ሩዲ ቮለር፣ ኔዝርላንዳዊው ማርኮ ቫን ባስተን፣ዴንማርካዊው ፍራንክ አንደርሰንና ስዊድናዊው ቶማስ ብሮሊን ከቀደሙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ከአሁን ዘመን ኮከቦቹ ደግሞ ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ስፔናዊው አልቫሮ ሞራታ፣ እንግሊዛዊው ዋይኒ ሩኒ፣ ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሂሞቪችና ቤልጂየማዊው ሮሜሎ ሉካኩን ማንሳት ማንሳት ይቻላል።

በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረው የ39 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሲሆን እስከ አሁን በተሳተፈባቸው አምስት የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች 25 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።

ፖርቹጋላዊው ኮከብ በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ለስድስተኛ ጊዜ በመሳተፍ አዲስ ታሪክ የጻፈ ሲሆን በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ በራሱ የተያዘውን የጎል ቁጥር ከፍ ሊያደርግ የሚችልበት እድል አለ።

ፈረንሳዊው ኮከብ ሚሼል ፕላቲኒ በ5 ጨዋታዎች 9 ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ፕላቲኒ ዘጠኙንም ግቦች ያስቆጠረው ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1984 ራሷ አዘጋጅታ ራሷ አሸናፊ በሆነችበት 7ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ነው።

እንግሊዛዊው ኮከብ አለን ሺረር፣ ፈረንሳዊው አንቶዋን ግሪዝማን እና ስፔናዊው አልቫሮ ሞራታ በተመሳሳይ ሰባት ግቦችን በማስቆጠር በግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የ31 ዓመቱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አምበል አልቫሮ ሞራታ ሰባተኛ ግቡን ያስቆጠረው በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አገሩ ክሮሺያን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ነው።

ሞራታ ስፔን በምታደርጋቸው ቀጣይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ከቻለ የጎል መጠኑን ከፍ ማድረግ ይችላል።

የ33 ዓመቱ አንቶዋን ግሪዝማን በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በፈረንሳይ ስብስብ ውስጥ ከተካተቱ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል።

ፈረንሳዊው ቲዬሪ ሄነሪ ፣ ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ ኔዘርላንዳዊውያኑ ፓትሪክ ክላይቨርትና ሩድ ቫኒ ስትሮይ፣ ቤልጂየማዊው ሮሜሎ ሉካኩ፣ እንግሊዛዊው ዋይኒ ሩኒና ፓርቹጋላዊው ኑኖ ጎሜዝ በአህጉራዊው መድረክ በተመሳሳይ 6 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ፈረንሳዊው ኮከብ ዚነዲን ዚዳን፣ ኔዘርላንዳዊው ማርኮ ቫን ባስተን፣ የቼክ ሪፐብሊኮቹ ሚላን ባሮሽና ፓትሪክ ሺክ፣ስፔናዊው ፈርናንዶ ቶሬስ፣ ጀርመናውያኑ የርገን ክሊንስማንና ማሪዮ ጎሜዝ፣ ፖላንዳዊው ሮበርት ሌዋንዶውስኪና የዩጎዝላቪያው ሳቮ ሚሎሴቪች በአህጉራዊው መድረክ በተመሳሳይ 5 ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፉ ተጫዋቾች ናቸው።

የ30 ዓመቱ የቼክ ሪፐብሊክ አጥቂና ፓትሪክ ሺክ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አገሩን ወክሎ ይጫወታል።

16 ተጫዋቾች በውድድሩ በተመሳሳይ 4 ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ከነዚህም ጀርመናዊው ሩዲ ቮላርና ገርድ ሙለር፣ ስዊድናዊው ሄነሪክ ላርሰን፣ ፈረንሳዊው ካሪም ቤንዚማ፣ እንግሊዛዊው ሀሪ ኬን፣ ስፔናዊው ዴቪድ ቪያ፣ ክሮሺያዊው ኢቫን ፔሪሲችና ስዊዘርላንዳዊው ዤርዳን ሻኪሪ ይጠቀሳሉ።

ክሮሺያዊው ኢቫን ፔሪሲችና ስዊዘርላንዳዊው ዤርዳን ሻኪሪ በ17ኛው አውሮፓ ዋንጫ አገራቸውን ወክለው እየተጫወቱ ነው።

ፈረንሳዊው ዩሪ ጆርካይፍ፣ ጣልያናውያኑ አንቶኒዮ ካዛኖና ማሪዮ ባሎቴሊ፣ ስፔናውያኑ ዴቪድ ሲልቫና ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ጀርመናዊው ማይክል ባላክ፣ ዌልሳዊው ጋሪዝ ቤልና ዴንማርካዊው ካስፐር ዶልበርግ በውድድሩ ላይ 3 ግቦችን ካስቆጠሩ ተጫዋቾች መካከል ይገኙበታል።

ዴንማርካዊው አጥቂ ካስፐር ዶልበርግ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አገሩን ወክሎ በመጫወት ላይ ይገኛል።

17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ 4ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በጨዋታዎቹ የሚቆጠሩ ግቦች በምንጊዜም የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃና የግብ መጠን ላይ ለውጥ ያስከትላል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም