የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት አስራ አንድ ወራት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አገበያየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት አስራ አንድ ወራት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን አገበያየ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2016 በጀት ዓመት አስራ አንድ ወራት 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኃይሉ ንጉሴ፤ ተቋሙ አገሪቱ ባሉት 25 ቅርንጫፎች ወደ ከ200 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት መቀበሉን ተናግረዋል።
በዚህም 23 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን ገልጸዋል።
ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቡና 18 በመቶ እንዲሁም የቅባት እህሎች 45 በመቶ ብልጫ እንዳላቸውና ሌሎችም በተመሳሳይ እድገት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ30 በመቶ እድገት አለው ነው ያሉት።
ምርት ገበያው አዳዲስ ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለውጭ ገበያ የሚውሉ ባቄላ፣ ኑግና ሽንብራ በቅርቡ በግብይት ሥርዓቱ ያስገባቸው አዳዲስ ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህን ምርቶች ከሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በምርት ገበያው እንዲሁም በውልና ኢንቨስትመንት እርሻ በኩል ለማከናወን አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
የቢራ ገብስ፣ ዳጉሳ፣ተልባ፣ቆዳና ሌጦ እንዲሁም የጥጥ ምርቶች ላይ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው የቢራ ገብስን መቀበል የሚያስችል ጥናት ተጠናቆ የግብይት ውል መጽደቁን ተናግረዋል።
በመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት 30 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ምርቶችን በመጋዘን በማከማቸት ከባንኮች ጋር ብድር የማመቻቸት ሥራ የተከናወነ ሲሆን ወደ 4 ሚሊዮን ብር ብድር መለቀቁን ጠቁመዋል።
የመጋዘን አገልግሎትን ለማስፋት የላብራቶሪ አቅምን በማደራጀት ከአንድ ምርት በላይ እንዲቀበሉ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ምርት ገበያው አገልግሎቱን ለማሳለጥ በከፈተው አካዳሚ በሰው ኃይል አቅም ግንባታና በምርምር ዘርፍ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው አካዳሚው ለአፍሪካም የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።
ምርት ገበያው በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግብይት የሚፈጽሙበት አሰራር ላይ የደረሰ ሲሆን በቀጣይ የተሻሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት እየሰራ ይገኛል።