ቀጥታ፡

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት  ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 10/2016 (ኢዜአ)፦በዘንድሮው አገር አቀፍ የክረምት  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ 39 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

የሰላም ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቅናቄ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

መርሀ-ግብሩ "በጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ቃል የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎች ማንም ሳያስገድዳቸው በፍላጎት ተነስተው ለማህበረሰባቸው አገልግሎት የሚሰጡበት መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ እሴቶችና ባህሎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው መሆኑን አመልክተው፤ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

የዘንድሮው መርሀ ግብር በ14 መስኮች አገልግሎቶች እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት እንደሚሰጥበት ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ፣የማዕድ ማጋራት፣ ትምህርትና  የጤና አገልግሎት ከሚሰጡ አገልግሎቶች መካከል ይገኙበታል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር ) ሚኒስቴሩ ዜጎች በሀገር ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስቻል ዋነኛ ስራው ነው ብለዋል።

መርሀግብሩ ዜጎች በመደጋገፍ ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑን ገልጸው፤ንቅናቄው ሰኔ 12 በአደዋ መታሰቢያ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ  የአብሮነትና የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጥበት መሆኑን አመልክተው፤በመርሀ ግብሩ 50 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አያይዘው ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በየጊዜው እያደገ የመጣ መሆኑንና የአንድ ጊዜ ዘመቻ ሳይሆን በሁሉም ጊዜያት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሸኔ መርሀ ግብሩ ከቁሳዊ ጥቅም ባለፈ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ከ 20 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በትምህርት በጤና እንዲሁም በተለያዩ የልማት ስራዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የ 2016 የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን ማስጀመራቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም