የጉዲና ቱምሳ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት መጀመር አካባቢው ያለውን ፍላጎቶችን የሚመልስ ታላቅ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጉዲና ቱምሳ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት መጀመር አካባቢው ያለውን ፍላጎቶችን የሚመልስ ታላቅ ተግባር ነው
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 9/2016 (ኢዜአ)፡- በነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ የጉዲና ቱምሳ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት መጀመር በአካባቢው ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶችን የሚመልስ ታላቅ ተግባር መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ በአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ጉዲና ቱምሳ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።
የፌዴራል፣ የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተከናወነው የበረራ አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የረጅም ዓመታት ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘቱን አስመልክቶ ደስታቸውን በይፋ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሰጠ ልዩ አቅጣጫ የፌዴራል መንግስትና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ በየቦታው ያሉ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ለአገልግሎት እንዲበቁ ክትትል እያደረጉና እየሰሩ መሆኑን ዛሬ የበረራ አገልግሎት የጀመረው የጉዲና ቱምሳ የአውሮፕላን ማረፊያ በማሳያነት ሊጠቀስ እንደሚችል ነው የተጠቆመው።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አውሮፕላን ማረፊያው የበረራ አገልግሎት መጀመሩ መንግስት ለህዝብ ለገባው ቃል በተግባር ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ማሳያ ነው።
መንግስት ለህዝቡ ለማሟላት ቃል የገባቸው የመሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች በተገቢው መንገድ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን ያሳየበት መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በመንግስትና ህዝብ መካከል መተማመንን እንደፈጠረ ጠቁመዋል።
ቀደም ብሎ በአካባቢው የጸጥታ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፤ መንግስትና ህዝብ በመተባበር የጸጥታ ችግሮችን አስወግደው የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት እንዲጀምር እንዳስቻሉም ተናግረዋል።
በዚህም መንግስት የህዝብ ጥያቄን ከመመለስ ባሻገር የአገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ተግባሩን ለማከናወን ምንም ዓይነት ችግር እንደማያግደው ማሳያ መሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
መንግስት በየትኛውም ችግር ውስጥ ሆኖ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ፣ ለአገልግሎት የማብቃት ስራ የሰራ መሆኑን የታየበት ፕሮጀክትም መሆኑን ነው ያብራሩት።
ህዝብ ለሚያቀርባቸው የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት ጥያቄዎች በተግባር ምላሽ የሚሰጥ መንግስት መኖሩን እንደሚያረጋግጥ የጠቆሙት ዶክተር ቢቂላ፤ ይህም በመንግስትና ህዝብ መካከል ያለውን ቅርርብ የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው በነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ መገንባት በአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር ገልጸው፤ በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶችን በተለይም አትክልት እና ፍራፍሬን በቀላሉ ለማዕከላዊ ገበያ በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳም አብራርተዋል።
መንግስት የአካባቢውን ህዝብ የልማት፣ የአገልግሎት፣ የሎጅስቲክስና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነትም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአውሮፕላን በረራ መጀመሩ የአካባቢው ህዝብ በማህበራዊ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነቱን እንደሚያጠናክረው ጠቁመው፤ በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፍ የሚኖረውን የአገልግሎት አቅርቦትና ፍትሃዊነት እንደሚያጎላው ገልጸዋል።
አካባቢው በባህል የበለጸገ፣ የቱሪዝም ሀብቱ ያለው መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ቢቂላ፤ የበረራ አገልግሎት መጀመሩ የህዝቡን ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።