የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ አለው- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻ አለው- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
ነቀምቴ፤ ሰኔ 09/2016 (ኢዜአ)፦የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መጀመር የአካባቢውን ግብርናና ኢንቨስትመንት እድገት ከማሳለጥ ባለፈ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እንደሚያሳድገው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የፌደራል፣ የኦሮሚያ ክልል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በአውሮፕላን ማረፊያው የበረራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው እንዳሉት የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ አገልግሎት መጀመሩ ለአካባቢው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በአካባቢው በረራው መጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያነሱት አፈ ጉባዔው፤ በተለይም የአካባቢውን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ እድገት ከማሳለጥ ባለፈ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ያሳድጋል።
አክለውም አውሮፕላን ማረፊያው መታሰቢያነቱ ለሀገራቸው መቆምን ባስተማሩን በቄስ ጉዲና ቱምሳ መሰየሙ የአሁኑ ትውልድም ለአገር ቆሞ የተሻለች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እንዲተጉ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው በክልሉ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚውሉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ናቸው ብለዋል።
በምስራቅ ወለጋ ዞን የተገነባውን የነቀምቴ ጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ እንደ አንዱ ማሳያ ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ የክልሉ መንግስት በቀጣይም ህብረተሰቡን በማሳተፍ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ግንባታ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጉዲና ቱምሳ አውሮፕላን ማረፊያ የአካባቢውን ነዋሪ የዓመታት ጥያቄ የመለሰ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ናቸው።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሀገር መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መካሄዱን የገለጹት አቶ መስፍን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማህበራዊ ትስስርን በመፍጠር ረገድ ከፍ ያለ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
አየር መንገዱ ከ20 በላይ የሀገር ውስጥ በረራዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ መስፍን፤ በውጭ አገር በረራም የአፍሪካ ኩራት ሆኖ ተደራሽነቱን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።
በበረራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው መንግስት ለዞኑ በሰጠው ትኩረት ብዙ የልማት ስራዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት እየበቁ እንደሚገኙ በመናገር በዚህም ትልቅ ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል።
የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ክብነሽ ተፈሪ እንዳሉት የወለጋና አካባቢው ህብረተሰብ ከተፈጥሮ ሀብቱ በሚገባ ተጠቃሚ እንዲሁን መሰል የልማት ፕሮጀክቶች ጉልህ ድርሻ አላቸው።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ብርሃኑ በንቲ አይሮፕላን ማረፊያው ከትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ለአካባቢው የልማት ምርቶች ማጓጓዣ ስለሚጠቅም አርሶ አደሩን እና የነጋዴውን ማህበረሰቡን የገቢ ሁኔታ የሚያሻሽል ነው ብለዋል።
በበረራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።