ቀጥታ፡

መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል አቅም ለኢኮኖሚ ልማት ለማዋል እድል የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል አቅም ለኢኮኖሚ ልማት ለማዋል እድል የፈጠረ መሆኑን ባለኃብቱ በላይነህ ክንዴ ገለጹ።  

መንግስት የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት በስፋት በመሳተፍ የልማት አጋርነታቸውን እንዲያረጋግጡ የፈጠራቸው ዕድሎች  ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ፤ ለ33 ዓመታት በዘለቀውና ከአነስተኛና ጥቃቅን ተነስቶ እስከ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት መሰረት የሚጥሉ ሥራዎችን ማከናወኑን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ሆቴል፣ ሪል ስቴትና የወጭና ገቢ ንግድ በስፋት በመሳተፍ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ እድል መፍጠሩንም እንዲሁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለግብርናው ዘርፍ በሰጡት ትኩረት መሰረት በአትክልትና ፍራፍሬ፤ በቡናና በቅባት እህሎች ልማት በመሰማራት ጥሩ አፈፃፀም አሳይተናል ነው ያሉት። 

መንግሥት የግል ባለኃብቱ በአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያለውን ጉልህ ሚና ታሳቢ በማድረግ ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማበረታቻዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁዋል። 

የተፈጠረውን ምቹ መደላድል በመጠቀም ባለሀብቶች ወደ ልማት በመግባት አገራቸውን የሚለውጡበት እድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው በቅርቡ በስፋት ያስተዋወቁትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ምርት ለአብነት አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ የሚሰራው ስራ ኢትዮጵያ በዓመት ለነዳጅ የምታወጣውን እስከ 6 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ በማስቀረት ወጭን ይቆጥባል ብለዋል።  

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የአየርና የድምጽ ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው መንግሥት የጀመራቸው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ይህንን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

መንግስት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሰጠው ትኩረትም የዘርፉን ተዋንያን ተሳትፎ ያሳድጋል ነው ያሉት። 

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመኪና ዕቃዎች መለዋወጫ የሚወጣን ገንዘብ በመቀነስ ረገድም አስተዋጿቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ በቀላሉ ቻርጅ የሚደረግ፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንድ ጊዜ ተሞልቶ በመቶዎች ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። 

ባትሪው እስከ ስምንት ዓመት ዋስትና ያለው መሆኑን ጠቅሰው በአገልግሎት ደረጃ ከዚያም በላይ የመቆየት አቅም እንዳለው ተናግረዋል።     

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ ማምረቻ ግብአቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ በመሆናቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተሽከርካሪዎቹን ባትሪ በአገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል አቅም በአግባቡ ለኢኮኖሚ ልማት ለማዋል እድል እንደሚፈጥር በመጠቆም፡፡

ድርጅታቸው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጀሮችን በማቅረብም ወደ አዲስና አዋጭ የቢዝነስ ዘርፍ ይሰማራል ብለዋል። 

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ከሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በላይ ለአገር ልማት የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ  በዚህ ረገድ ያለውን ጅምር ማስፋት ይገባል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም