ስፖርትን ከውድድርነት በተጓዳኝ ለገጽታ ግንባታና ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጀት እየተሰራ ነው- አምባሳደር መስፍን ቸርነት - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርትን ከውድድርነት በተጓዳኝ ለገጽታ ግንባታና ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጀት እየተሰራ ነው- አምባሳደር መስፍን ቸርነት
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2016 (ኢዜአ)፦ ስፖርትን ከውድድርነት በተጓዳኝ ለገጽታ ግንባታና ዲፕሎማሲ ለመጠቀም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጀት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
ስፖርት ከውድድርነት ባሻገር አገርን በበጎ መልኩ ለማስተዋወቅና ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ሚናው የጎላ ሲሆን፤ አገራት ይህን የግንኙነት አማራጭ በስፋት ይጠቀሙበታል።
የስፖርት ዲፕሎማሲ የባህልና ቋንቋ ልዩነቶችንና ድንበሮችን በመሻገር በሕዝቦች መካከል መቀራረብን የመፍጠር አቅሙ ጠንካራ ነው።
ስፖርተኞች እንዲሁም ስፖርት ተቋማትና ደጋፊዎች በስፖርታዊ ሁነቶች ላይ የአገራቸው አምባሳደር በመሆን የሚያከናውኗቸው ማህበረሰባዊ ትብብርን የማጎልበት አቅሙ ከፍተኛ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በስፖርት ፖሊሲውና በሌሎች ስትራቴጂክ ሰነዶች ስፖርት ለዲፕሎማሲና ቱሪዝም እድገት እንዲውል በግልጽ መቀመጡን ይገልጻሉ።
በዚህም አማካኝነት ስፖርት ዲፕሎማሲን የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ ገጽታን ለመገንባትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ እየተሰራበት እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቶች የስፖርት ዲፕሎማሲው በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል፡፡
አትሌቶቹ በተለያዩ አህጉራት ኢትዮጵያን ወክለው በሚወዳደሩበት ወቅት ከሚያስመዘግቡት ድል ባለፈ የአገሪቷን ባንዲራ ከፍ በማድረግ በጎ ገጽታዋን እንደሚያስተዋውቁ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ አገርና የጀግኖች አትሌቶች መፍለቂያ መሆኗንም አጉልተው እንደሚያሳዩ ነው አምባሳደር መስፍን የገለጹት።
የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የስፖርት ዲፕሎማሲ ስራዋን የምታከናውንበት ትልቁ ስፖርታዊ ሁነት እንደሆነና በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ አገራት ሉላዓዊነታቸውን ፣ነጻነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
ከአትሌቲክስ ውጪ በወርልድ ቴኳንዶ፣ካራቴና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በምትሳተፍባቸው ሌሎች ስፖርቶችም የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ የሚገነቡ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም በመጠቆም።
ይሁንና ከስፖርት ዲፕሎማሲ አቅም አንጻር የተከናወኑ ስራዎች በቂ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፤ በባለድርሻ አካላት ትብብር የላቀ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
ለዚህም በቀጣይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የስፖርት ዲፕሎማሲውን አቅም ይበልጥ ለመጠቀም በሚያስችሉ ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።