የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 9/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ቀን መርሐ ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ወላይታ ድቻ ከሀድያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 3 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ግቦችን አስተናግዷል። ወላይታ ድቻ በ29 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሀድያ ሆሳዕና ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 1 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
በ5ቱ ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 6 ግቦች ተቆጥረውበታል።
በግርማ ታደሰ የሚሰለጥነው ሀድያ ሆሳዕና በ35 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሻሸመኔ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሻሸመኔ ከተማ ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 4 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ በ14 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በአንጻሩ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ያለፉት 5 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አሸንፏል። በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 15 ግቦችን ሲያስቆጥር የተቆጠረበት 1 ግብ ብቻ ነው።
በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ34 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የፕሪሚየር ሊጉ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ሃዋሳ ከተማን 5 ለ 0 እንዲሁም ሲዳማ ቡና ሀምበሪቾን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።