አምስቱ ጣሊያናውያን አሰልጣኞች በአውሮፓ ዋንጫ  

በይስሐቅ ቀለመወርቅ

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው 17 ኛው የአውሮፓ ዋንጫ፤ ሦስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን የምድብ ጨዋታዎች እየተደረጉ ነው።

ከጨዋታዎቹ ጎን ለጎን  ደግሞ የተለያዩ አስደናቂ ቁጥራዊ መረጃዎች እየተመዘገቡበት ነው።

ከነዚህም ውስጥ 24 ሀገራትን ከሚያሰለጥኑት አሰልጣኞች አምስቱ ጣሊያናውያን መሆናቸው፤ የዘንድሮውን የአውሮፓ ዋንጫ ልዩ ያደርገዋል።

እነዚህ አሰልጣኞች እነማናቸው የሚለውን ደግሞ እንደሚከተለው እንመልከት፡-

ሉቺያኖ ስፓሌቲ፡- ይህ ጣሊያናዊ የ65 ዓመት አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመኑ የአማካይ ሥፍራ ተሰላፊ ሲሆን፤ የአሰልጣኝነት ጊዜውን የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን አሳልፏል። 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም የጣሊያኑን ክለብ ኢምፖሊ በማሰልጠን የአሰልጣኝነት ጉዞውን አንድ ብሎ ጀመረ። ከዛም የጣሊያን ክለቦች የሆኑትን ሳምፕዶርያ፣ቬንዚአ፣ ዩዲኒዜ፣ አንኮና፣ ሮማ፣ኢንተርሚላን እና ናፖሊን አሰልጥኗል። 

በክለብ አሰልጣኝነት ቆይታውም ሮማን ሁለት ጊዜ የኮፓ ኢታልያ ተከታታይ የዋንጫ ድል ሲያበቃ፤ ናፖሊን ደግሞ አምና የጣሊያን ሴሬአ ዋንጫን እንዲያነሳ አድርጎታል። የሩሲያውን ክለብ ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግንም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2014 በማሰልጠን ሁለት ጊዜ የሩሲያን ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን እንዲያነሳ አድርጎታል። 

በነሐሴ ወር 2024 ላይ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመ ሲሆን፤በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአውሮፓ ዋንጫ የጣሊያን ብሔራዊ ቡድንን ለውድድር ይዞ ቀርቧል።

ቪሴንዞ ሞንቴላ ፡- ይህ ጣሊያናዊ የ49 ዓመት አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመኑ በአጥቂ ሥፍራ ይጫወት የነበረ ሲሆን፤ አሰልጣኝነት የጀመረውም በተጨዋችነት ዘመኑ ለተጫወተለት ሮማ ጊዜአዊ አሰልጣኝ ሆኖ በማሰልጠን ነበረ። 

ከዛም የጣሊያኖቹን ክለቦች ካታኒያ፣ ፊዮረንቲና፣ ሳምፕዶሪያና ኤሲሚላንን ካሰለጠነ በኋላ ወደ ስፔኑ ክለብ ሲቪያ በማምራት አሰልጥኗል። በመጨረሻም ወደ ተርኪዬ ሱፐርሊግ በመሄድ የተርኪዬን ክለብ አዳና ዲሚስፖር ካሰለጠነ በኋላ፤ የተርኪዬ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ እያሰለጠነ ይገኛል። 

የተርኪዬ ብሔራዊ ብድን፤በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ባሳየው ብቃትና አሁን ላይ ባለው ወቅታዊ አቋም ያልተጠበቀ መልካም ጉዞ ያደረርጋል የሚል ግምት፤ በእግር ኳስ ተንታኞች እየተሰጠው ይገኛል። 

ዶሚኒኮ ቲዴስኮ፡- ይህ 38 ዓመት ጣሊያናዊ አሰልጣኝ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 በጀርመኑ ክለብ ኤያትዝበርገር አወ ማሰልጠን የጀመረ ሲሆን የጀርመኖቹን ክለቦች ሻልክ 04 እና አርቢ ላይፕዚግንም አሰልጥኗል። የሩሲያው ክለብ ስፓርታክ ሞስኮን ማሰልጠን ችሏል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2023 የቤልጂየምን ብሔራዊ ቡድን እንዲያሰለጥን የተሾመ ሲሆን፤ በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአውሮፓ ዋንጫ፤ ወርቃማ ትውልዳቸውን አባክነው አዲስ ቡድን ይዘው የመጡትን ቤልጂየሞች በውጤት ለመካስ ብዙ ይጠበቅበታል።

ማርኮ ሮሲ፡- ይህ የ65 ዓመት ጣሊያናዊ አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመኑ በተከላካይ ሥፍራ የተጫወተ ሲሆን፤ የአሰልጣኝነት ሥራውን የጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የጣሊያኑን ክለብ ሉማዜኒ በማሰልጠን ነበር። ከዛም የጣሊያኖቹን ክለቦች አውሮራ ፕሮ ፓትሪያ፣ ስፔዚያ፣ ስካፋቲሴ እና ካቪዜ የተባሉትን ክለብ  አሰልጥኗል። 

ከዛም የሀንጋሪ ክለብ የሆነውን ቡዳፔስት ሆንቭድ እና የስሎቫኪያውን ክለብ ዱናስካ ስትሪዳን

ያሰለጠነ ሲሆን፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 የሀንጋሪ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ተሾሟል። 

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአውሮፓ ዋንጫ፤ ማርኮ ሮሲ የሀንጋሪ ብሔራዊ ቡድንን ይዞ እተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው፤ በስዊዘርላንድ 3 ለ1 ተሸንፏል። 

ፍራንቺስኮ ካልዞና፡- ይህ የ55 ዓመት ጣሊያናዊ አሰልጣኝ በተጨዋችነት ዘመኑ በአማካይ ሥፍራ የተጫወተ ሲሆን የአሰልጣኝነት ሕይወቱን በአብዛኛው በረዳት አሰልጣኝነት አሳልፏል። 

የአሰልጣኝነት ስራውን የጀመረው የጣሊያኑ ክለብ ፔሩጂያን በማሰልጠን ሲሆን በጣሊያኖቹ ክለቦች አሌሳንድርያ፣ሶሬንቶ፣ ኢምፖሊ፣ ናፖሊ እና ካግሊያሪ፣ በረዳትነት አሰልጣኝነት አገልግሏል።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ የስሎቫኪያን ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝነት እየመራ ይገኛል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም