ቀጥታ፡

መንግስት የኮሪደር ልማቱን በተሳካ መልኩ በማከናወን ቃሉን በተግባር ፈጽሟል-የልማት ተነሽዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የኮሪደር ልማቱን በተሳካ መልኩ በማከናወን ቃሉን በተግባር መፈጸሙን የአራት ኪሎ እና የፒያሳ የልማት ተነሽዎች ተናገሩ።

የልማት ተነሽዎች በፒያሳ እና አራት ኪሎ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የልማት ተነሽ ጎብኝዎች በጉብኝታቸው ወቅት ባዩት ነገር መደነቃቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ከቦታው ሲያነሳቸው ስፍራው ለኮሪደር ልማት የተፈለገው የከተማዋን ደረጃ ለማሻሻል እና የነዋሪዎችን ህይዎት ለመቀየር እንደሆነና በአጭር ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ እንደገለጸላቸው አውስተዋል።


 

በቃሉ መሰረትም የከተማዋን ገፅታ የለወጡ፣ የሚያውቁትን አሮጌ ሰፈር ያስዋቡ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን ተመልክተናል ነው ያሉት።

በፒያሳ እና አራት ኪሎ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለልማት ከአካባቢው ሲነሱም ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን ገንብቶ በማስረከብ የተሻለ ኑሮ እንድንኖር አድርጎናል ነው ያሉት።

በልማት ምክንያት ከመነሳታቸው በፊት ይኖሩበት የነበረው ደሳሳ ቤት ከመሆኑ የተነሳ የክረምት ዝናብ እና የበጋ ጸሃይ ይፈራረቅባቸው እንደነበርም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን መሰረተ ልማቱ በተሟላለትና ውብ በሆነ ሰፈር በተገነባላቸው መኖሪያ ቤት የተሻለ ህይወት ጀምረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም