ቀጥታ፡

አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ትውልድ የማነጽ ተልዕኮውን ለመወጣት የገጠመውን የፋይናንስ እጥረት  ለማቃለል ለበጎ አድራጊዎች ድጋፍ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ትውልድ የማነጽ ተልዕኮውን ለመወጣትና ተቋማዊ አቅሙን ለማደራጀት የገጠመውን የፋይናንስ ዕጥረት  ለማቃለል ለበጎ አድራጊዎች ድጋፍ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዛሬ ባካሄደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔው የአባላት መዋጮ እና የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ ለማህበሩ የሚበጁ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በ1952 ዓ.ም የተመሰረተው አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ዕውቀት ለትውልድ ለማሻገር የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ጀማሪ ፀሐፍትን በማሰልጠን፣ በንባብ ንቅናቄ፣ በአባላት መረጃ ማደራጀትና ዕውቅና አሰጣጥ፣ በመፅሐፍት ዐውደ ርዕይ ተሳትፎና በልዩ ልዩ ሙያዊ ድጋፎች ማህበራዊ ኅላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን ማህበሩ የሚጠበቅበትን ትውልድ የመገንባት ሀገራዊ ሚና ለመጫወት የፋይናንስ ዕጥረት ችግር ዛሬም ያልተሻገረው ዐብይ ተግዳሮት እንደሆነ አንስተዋል።

ችግሩን ለማቃለልም የራሱን ገቢ ማመንጫ የሚሆን 'የብዕር አምባ' የተሰኘ ባለሰባት ወለል ሁለገብ ሕንፃ ለመገንባት በ2008 ዓ.ም ከሊዝ ነጻ ቢረከብም በገንዘብ እጦት ሳቢያ ዕቅዱን ዕውን ማድረግ አልቻለም  ብለዋል።


 

ሲኤምሲ አካባቢ በተረከበው መሬት ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጫ ሕንጻ መገንባት ባይችልም መሬቱን ግን በባለቤትነት ማቆየት መቻሉን ተናግረዋል።

ማህበሩ ወደፊት የተሻለ ማዕከል እስኪገነባ ድረስ በከተማ አስተዳደሩ ትብብር እና በበጎ ፈቃደኛ ግለሰብ ድጋፍ ለጊዜያዊነት አገልግሎት የሚውል ባለዜሮ ወለል ሕንጻ ግንባታ ማስጀመሩን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ ያለው ሕንፃ የገቢ ማስገኛ ሱቆች፣ ቢሮዎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ቤተ መፅሃፍት ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕንጻው ሲጠናቀቅ ማህበሩ ራሱን ለማጠናከርና የአባላቱን እንግልት እንደሚያቃልል ገልጸው፤ በጠቅላላ ጉባኤውም የገቢ አሰባሳቢና የህንፃ ኮሚቴ እንዲዋቀር መወሰኑን ገልጸዋል።

ከማህበሩ አባላት መካከል ደራሲ የምወድሽ በቀለ እና ዶክተር ታደለ ገድሌ ትውልድ ማነጽ የሚቻለው የንባብ ባህል እና ስነ- ጽሁፍ ሲዳብር መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሀገራት የሰለጠኑት በጥበብና ዕውቀት የተካነ ትውልድ በመገንባት መሆኑን ገልጸው፣ አዕምሯዊ ልማትን ለማጎልበት ባለሀብቶች እና የስነ -ጽሁፍ ማህበረሰብ  የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንዳለበት ገልጸዋል።

ማህበሩ በትውልድ ግንባታ ላይ የሚያከናውናቸው ተግባራት እንዲያሳኩ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ማህበሩን ራሱን ለመቻል የሚያደርጋቸውን ስራዎች መደገፍ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል።

 

 

 
 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም