ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች /ኤር ትራክተርስ/ ስራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ አምስት ዘመናዊ  የርጭት  አውሮፕላኖች /ኤር ትራክተርስ/ በይፋ ስራ አስጀመሩ።

በይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የናሽናል ኤር ዌይስ አመራሮች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝና ሌሎች አደጋዎችን ለመቆጣጠር የራሷ የኬሚካል ርጭት  አውሮፕላኖች ስላልነበራት ለኪራይ እስከ 13 ቢሊየን ብር ወጪ ስታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የአደጋ መቆጣጠሪያ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች  እንዲኖራት ይደረጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም መንግሥት አምስት ዘመናዊ የኬሚካል ርጭትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ ኤር ትራክተሮችን ግዥ ፈጽሞ በዛሬው ዕለት በይፋ ስራ አስጀምሯል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ  በዚህ ወቅት፥ ከዚህ ቀደም የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የደን ቃጠሎና የግሪሳ ወፍን መቆጣጠር የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ባለመኖሩ  በሰው ኃይል በባህላዊ መንገድ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በሰሜን ተራሮችና በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ቃጠሎ ባጋጠመ ጊዜ ኢትዮጵያ በልመና እና በኪራይ ከሌሎች አገራት የርጭት አውሮፕላኖችን በማምጣት ስትጠቀም መቆየቷን አውስተዋል።

አሁን ላይ መንግስት አደጋን በራስ የመቋቋምና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አካል ያደረገውን የአምስት ኤር ትራክተሮች ( የርጭት አውሮፕላኖችን) ገዝቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የኤር ትራክተር ባለቤት መሆኗ የጸረ አረምና ጸረ ተባይ የኬሚካል ርጭትን፣ የበረሃ አንበጣ መከላከልን፣ የስንዴና መሰል ሰብሎች የዋግ በሽታን ለመከላከል ትልቅ ሀገራዊ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

አውሮፕላኖቹ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት  የመስጠት አቅም ያላቸው በመሆናቸው እንደ እሳት ያሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በፍጥነት ምላሽ መስጠት እንደሚያስችሉም አንስተዋል።

አውሮፕላኖቹ ከኢትዮጵያ ባለፈም ለጎረቤት ሀገርና ለሌሎችም ጥቅም መስጠት የሚችሉ ናቸው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እውቀትና ቴክኖሎጂ የግብርና መር ስራን ለመተግበር በሂደት ላይ መሆኗን አንስተዋል።

ከ2011 ሰኔ ወር ጀምሮ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በስምንት ክልሎች 235 ወረዳዎችን ማዳረሱንና ሰፊ ጉዳት ማስከተሉን ጠቅሰው፥ የራሳችን የኬሚካል ርጭት አውሮፕላን ባለመኖሩ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራውም ሶስት ዓመት መውሰዱን ተናግረዋል።

በኪራይ ለመጡ አውሮፕላኖችና ለኬሚካል ርጭት 13 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን  አውስተው፥ አሁን ላይ በ850 ሚሊዮን ብር 5 ኤር ትራክተሮችን በመግዛት ሀገራዊ አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል።

ይህም ተጋላጭነትን ለመቀነስ፣ አደጋ ሲፈጠርም ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ለሌሎች ተቋማትና ሀገራት እንድንደርስ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሀገር በቀሉ ናሽናል ኤርዌይስ ኤር ትራክተሮቹን የማስተዳደር ስራውን በጨረታ መረከቡን ጠቅሰዋል።

ከመደበኛ ስራቸው በተጓዳኝ ለሰፋፊ የንግድ እርሻ ልማት የኬሚካል ርጭት፣ ለእሳት አደጋና ሌሎችም ስራዎች በኪራይ ጥቅም ላይ ውለው ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገኙ የሚያደርግ ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

 ለአብነትም ከኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽንና ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር አውሮፕላኖቹን ለርጭት መጠቀም የሚያስችል ስምምነት ዛሬ መፈረሙን በማንሳት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም