ማዕከሉ በአራት ክልሎች የአየር ትንበያ መረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ በአራት ክልሎች የአየር ትንበያ መረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
ሶዶ፣ ሰኔ 8 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የደቡብ አገልግሎት ማዕከል በአራት ክልሎች ወቅቱን የጠበቀ የአየር ትንበያ መረጃ ተደራሽነት በማስፋት ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
ማዕከሉ የክረምት ወቅት አየር ትንበያን በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በወላይታ ሶዶ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የማዕከሉ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው አየለ እንዳሉት፤ ማዕከሉ የአየር ትንበያ መረጃን በማጎልበት ለልማት ስኬታማነት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እየሰራ ነው።
ለዚህም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ተናግረዋል።
የግብርና ልማት ውጤታማነት፣ የአየር ሁኔታን ተከትሎ የሚከሰቱ በሽታዎችና የተፈጥሮ አደጋን ከመቀነስ አኳያ ወቅታዊ የአየር ሁኔታ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ስልጠናውም ከአየር ትንበያ መረጃ ተደራሽነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማሻሻል እንደሚረዳ አቶ ከፍያለው አስረድተዋል።
ማዕከሉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ፣በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በሲዳማ ክልሎች በመጪው ክረምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
ይህም ለመኸር እርሻ ሥራዎች ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ተቋማት የአየር ትንበያ መረጃ በመለዋወጥ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል ተደራሽነቱን ለማስፋት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ተወካይ አቶ ሙሉነህ ዓለማየሁ በበኩላቸው ከኢንስቲትዩቱ ጋር ባለን ቅንጅታዊ አሠራር የበልግ ግብርናን ማሳካት ችለናል ብለዋል።
በመኸር ግብርናም እንዲሁ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከአየር ፀባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚቲዎሮሎጂና የሃይድሮሎጂ ፋኩልቲ ዲን ታደሰ ቱጁባ(ዶ/ር) ናቸው።
በበክረምቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችና በሲዳማ ደጋማ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ለመስኖና ለሃይል ማመንጫነት የሚውል ውሃ ለመያዝ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በስልጠናው ከአራቱ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።