በአቪዬሽን ሙያ መስክ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት ለዘርፉ የላቀ እድገት እንተጋለን - አቶ ካሴ ይማም - ኢዜአ አማርኛ
በአቪዬሽን ሙያ መስክ ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት ለዘርፉ የላቀ እድገት እንተጋለን - አቶ ካሴ ይማም
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦በአቪዬሽን ሙያ መስክ ብቁ የሰው ሃይልን በማፍራት ለዘርፉ የላቀ እድገት እንተጋለን ሲሉ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ካሴ ይማም ገለጹ።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ መስተንግዶ፣ በንግድና በአውሮፕላን ጥገና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 787 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
ከእነዚህም ውስጥ 142 የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ 308 የአውሮፕላን ጥገና ሙያተኞች፣ 297 የበረራ አስተናጋጆች፣ 25 የኤሌክትሮ ሜካኒካልና 15 የንግድና ደንበኞች አገልግሎት ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሃላፊ አቶ ረታ መላኩ ፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ካሴ ይማም እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ታድመዋል።
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ካሴ ይማም በዚሁ ወቅት፤ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ብቃት ያላቸውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ረገድ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል ።
ዩኒቨርሲቲው በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ መስተንግዶ፣ በኤሮኖትካል ኢንጂነሪንግ፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በንግድና ሽያጭ ዘርፍ የሰለጠነ ሙያተኛን በማፍራትና በማብቃት ወደ ስራ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
መጪው ጊዜ በአፍሪካ የአቪዬሽን ሴክተር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአቪዬሽን ሙያ መስክ ብቁ የሰው ሃይልን በብዛት በማፍራት ለዘርፉ የላቀ እድገት እንተጋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሃላፊ አቶ ረታ መላኩ በበኩላቸው፣ አየር መንገዱ በአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በኩል በየጊዜው በርካታ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ወደ ተቋሙ እያስገባ መሆኑን አንስተዋል።
ተቋሙ በአቪዬሽን ዘርፍ የአውሮፕላን አብራሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሙያተኞችን በማሰልጠን ረገድ የተዋጣለት ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ይህም አየር መንገዱ እያደገ እንደመጣ ማሳያ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ወደ ስራ ሲገቡም ሀገርንና ተቋማቸውን በሚገባ እንዲያገለግሉና በተለይም ለስራ ላይ ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በዕለቱ ከተመረቁ የአውሮፕላን አብራሪዎች መካከል የማዕረግ ተመራቂዋ ሰልጣኝ ካፒቴን ፌቨን መሰረት አየር መገዱ በሰጣት የስራ ሃላፊነት በትጋትና በቅንነት ሀገሯን እንደምታገለግል ገልጻለች።
ሌላኛው የማዕረግ ተመራቂ ካፒቴን ኤርሚያስ ሙላቱ አየር መንገዱ ትጋትና ጥራት በተሞላበት መንገድ ስልጠናውን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጾ፤ ይህም በሙያው ትልቅ አቅም እንድገነባ አድርጎኛል ብሏል።
በቀጣይም የአውሮፕላን አብራሪዎችን የማሰልጠን እድል በማግኘቱ ይህን ሙያ ሰልጣኞች በብቃት እንዲወስዱት ለማድረግ በሃላፊነት እንደሚሰራ ገልጿል።
በኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩንቨርሲቲ ተምራ በበረራ መስተንግዶ የተመረቀችው ካሜሮናዊቷ ቺናን ቼልሲ በበኩሏ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእርግጥም ግዙፉና አፍሪካዊ ተቋም መሆኑን በቆይታዋ እንደተገነዘበች ገልጻለች።
በቀጣይም በሙያዋ ለዚሁ አየር መንገድ መስራት ህልሟ እንደሆነም ገልጻለች።
ከተመራቂዎቹ መካከል ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ሰልጣኞች ይገኙበታል።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ ግሩፕ በየጊዜው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያሰፋ የአውሮፕላን ቁጥር እየጨመረና ብቁ የሰው ሃይል እያፈራ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።