ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስር በመፍጠር በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የድርሻዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር በመፍጠር በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኗን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ኃብት አጠቃቀም 3ኛው የአፍሪ ራን የዓባይ ወንዝ ፍትሕዊ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስር ዓመታዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 

መድረኩ "የጋራ ኃብት ለጋራ የወደፊት የተሻለ ዕጣ ፋንታና ብልጽግና፤ የዓባይ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ለትብብርና ቀጣናዊ ትስስር " የሚል መሪ ሃሳብ ተሰጥቶታል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)፤ በአፍሪካ ቀንድ በርካታ የዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች በመኖራቸው ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ምክንያት ሆኗል ብለዋል። 


 

በዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር በመፍጠር ለአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ሰላምና መረጋጋት የራሷን ድርሻ እየተወጣች እንደምትገኝ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚፈጥረው ቀጣናዊ የኃይል ትስስርም በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ዓይነተኛ ሚና የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል።

በአብነትም ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እንዲሁም ለኬንያ ዝቅተኛ የታሪፍ ክፍያ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ሰላምና ደኅንነትን የመፍጠር ዓላማ ያነገበ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና የአፍሪካ ቀንድ አገራትን በኃይል በማስተሳሰር በትብብር ላይ የተመሠረተ ቀጣናዊ ዕድገትና ብልጽግናን ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የዓባይ ወንዝ ውሃን በፍትሃዊና ምክንያታዊነት ለመጠቀም የተፋሰሱን አገራት ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የአገራትን ትብብር ማጠናከርም ለቀጣናዊ የኢኮኖሚና አካባቢ ዘላቂ ልማትን ለማሳለጥ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታም ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ በአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ትብብርና የኃይል ትስስርን በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ መድረኩ በላይኛውና የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገራትና ማኅበረሰብ መካከል ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ ተጠቃሚነት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል። 


 

የውሃ ኃብት አጠቃቀም ምሁራን በዓባይ እና በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚያነሷቸው በዕውቀትና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሃሳቦች የጋራ አረዳድ ለመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

መሰል ሙያዊ የምክክር መድረኮችም ሃሳብን በሃሳብ በመሞገት በትብብር ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር ቀላል የማይባል ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። 

በመድረኩ ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ የተፋሰሱ የውሃ ኃብት አጠቃቀም ሙያተኞች፣ የውጭ ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራን እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትብብር በተዘጋጀው መድረክ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ያለፉት 14 ዓመታት የውሃ አስተዳደር ሂደት፣ የውሃ ኃይል አማራጭ ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖና የዓባይ ተፋሰስ የተጽዕኖ የቅነሳ ስትራቴጂክ ስልቶችን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም