ቀጥታ፡

በፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት መላመድ ሳቢያ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የዘርፉ ተዋንያኖች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ):- የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል የዘርፉ ተዋንያኖች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን  ገለጸ።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ ማኅበር  12ኛው ሀገር አቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መላመድ ሳቢያ እያስከተሉ ያለውን ችግሮች መቅረፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ ምክንያት በጤናው ዘርፉ ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖና ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላቶች ምን ሚና መጫወት አለባቸው?  በሚል ርዕሰ-ጉዳይ የመወያያ ጽሑፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የመድኃኒት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ እንዳሉት፤ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ከጀርሞች መላመድ በጤናው ዘርፍ ላይ ተግዳሮት እየሆኑ ከመጡ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም መንስኤ ከሆኑት ውስጥ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ለማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አለመሰራታቸው ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች በየጊዜው አቅማቸውን የሚያጎለብቱ ተግባራትን በሚፈለገው ደረጃ አለመከናወን እንዲሁ።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድም መድኃኒቶች በሽታን የመፈወስ አቅማቸውን የሚያዳክም በመሆኑ ይህም በሀገሪቱ ብሎም በማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ችግሩ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ  የመድኃኒቶችን  ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነታቸውን የማረጋገጥና የባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት  ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት የጀርሞች መላመድ ችግርን ለመቀነስ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት  ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ችግሩን በተጠናከረ መልኩ ለመፍታት በዘርፉ ላይ የሚገኙ ተቋማቶች የጀመሯቸውን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክረው መሄድ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ የፋርማሲ  ማኅበር  ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ሰይፉ፤ ማኅበሩ  በዛሬው እለት 12ኛው ሀገር አቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን ቀን ከተለያዩ  ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አክብሯል ብለዋል።

ማኅበሩም የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ  እያሳደረ ያለውን ጫና ለመከላከል የፋርማሲስት ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በተለያዩ ጊዜያት ለባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ  ቆይቷል ብለዋል።

በተጨማሪም የፋርማሲ ባለሙያዎች በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ላይ  የስነ-ምግባር ደንብ ተከትለው እንዲሰሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አክለዋል።

የፀረ-ተህዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድ ምክንያት እያስከተለ ያለውን የጤና ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ዜጋ ብሎም ተቋማቶች የየራሳቸውን  የቤት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ከእነዚህ አካላቶች ውስጥ የፋርማሲስት ባለሙያዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ የፀረ- ተህዋሲያን መድኃኒቶችን በአግባቡ እንዲወስዱ በቂ ግንዛቤ በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም