ቀጥታ፡

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄያችን ምላሽ ማግኘት በመጀመሩ ተደስተናል-የቡልጋ ከተማ ነዋሪዎች

ደብረ ብርሃን ፤ ሰኔ  8 / 2016 (ኢዜአ)፡- ለክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር  ያቀረብነው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄያችን በአጭር ጊዜ ምላሽ ማግኘት በመጀመሩ  ተደስተናል ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን  የቡልጋ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለጹ።

የሰሜን ሸዋ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብሏል።

የቡልጋ  ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ ጉልላት ሀብቴ  እንዳሉት ፤በከተማዋ ባለሃብቶች መዋለ ነዋያቸውን በማፍሰስ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጓት ነው።

ሆኖም   የከተማዋን አድገት የሚመጥን የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ  ነዋሪውና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መቸገራቸውን ገልጸዋል። 

በቅርቡ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ጋር በተደረገው ውይይት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ኃይሉ አውግቸው እንደተናገሩት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ ሲጎበኙ በተካሄደው ውይይት ህዝቡ ካነሳቸው ጥያቄዎች ዋናው የውሃ አቅርቦት ችግር ነበር።

ርዕሰ መስተዳድሩ የነዋሪዎችን መሰረታዊ ችግር በማዳመጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠታቸው በአዲስ መልክ የተደራጀው አመራር  ችግራችንን ለመፍታት ቆርጦ መነሳቱን ማሳያ ነው ብለዋል።

ወይዘሮ አፀደ ጌታሁን ፤ በከተማዋ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ጠቅሰው ከርዕሰ መስተዳድሩ  ጋር ከተደረገው ውይይት  በኋላ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የዘመናት ችግራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ አግኝቶ የውሃ መስመር ዝርጋታና ሌሎች ሥራዎች በመጀመራቸው ተደስተናል ብለዋል።

በክልሉ መንግሥት በተመደበው በጀት ግንባታው በፍጥነት ተጠናቅቆ  የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆን ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ አደርጋለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ተወካይ አቶ ሙላት ፍቅሬ፤  ርዕሰ መስተዳድሩ የቡልጋ  ከተማ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። 

የክልሉ መንግሥት በመደበው በጀት በጅምር ላይ የነበሩት የ10 ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የዋና ዋናና የውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታ፣ ስድስት የውሃ ማከፋፈያ ቦኖዎችና ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውሃ መስመር ዝርጋታው ቀደም ሲል የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶችን ወደ ሥራ በማስገባት ከ30ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የመስመር ዝርጋታውና ተያያዥ ሥራዎችን እስከዚህ ወር መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሙላት ተናግረዋል።

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ከ479 ሚሊየን  ብር በላይ በጀት ንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ግንባታ፣ ማሻሻያና ማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተሰራ መሆኑን የመምሪያው መረጃ ያሳያል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም