በማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞችን ጨምሮ በመደበኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የዝግጅት ስራ ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞችን ጨምሮ በመደበኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የዝግጅት ስራ ተጠናቋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦ በማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞችን ጨምሮ በመደበኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ገለፀ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከአስር ዓመት በፊት በ 13 ወረዳዎች የተጀመረው የጤና መድህን አገልግሎት አሁን ላይ 55 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአባላት አስተደደር ሃብት አሰባሰብ መሪ ስራ አስፈጻሚ ጉደታ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ መነሻነት በኢትዮጵያ ሁለት አይነት የማህበረሰብ አቀፍ እና የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ተደርጓል።
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን መደበኛ ባልሆነ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ አርሶና አርብቶ አደሮች የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት የመንግስት ሰራተኞች፣ ጡረተኞችን ጨምሮ ሌሎች በመደበኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የዝግጅት ስራው መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
አገልግሎቱ በመጀመሪያው ዙር 3 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ አባላትን በማካተት በተለይ የመንግስት ሰራተኞችን እና ጡረተኞችን የማህበራዊ ጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ የዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
ይህንን እውን ለማድረግ በየተቋማቱ የሰራተኞችን ብዛትና የደመወዝ መጠን የሚገልጽ መረጃ የማደራጀት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ ማህበራዊ የጤና መድህንን ለመጀመር ዝግጅቱን በማጠናቀቅ፤ የመንግስትን አቅጣጫ በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
አገልግሎቱ በተለይም ከመድሃኒት እጥረት ጋር ተያይዞ እየገጠመ ያለውን ችግር ለመፍታት ከከነማ እና ከቀይ መስቀል ጋር ውሎችን በመዋዋል የጤና መድህን አባላቶች መድሃኒት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡