መቻል ስፖርት ክለብን በአምስት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች አንዱ ለማድረግ እየሰራን ነው - የመቻል ስፖርት ክለብ ቦርድ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016 (ኢዜአ)፦ የመቻል ስፖርት ክለብን የቀደመ ክብርና ዝና በማደስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ምርጥ 10 ክለቦች አንዱ የማድረግ ራዕይ ተሰንቆ እየተሰራ መሆኑን የመቻል ስፖርት ክለብ የቦርድ አመራሮች ገለጹ።

መቻል የመከላከያ ሰራዊቱን የድል አድራጊነት ክብር የተላበሰ እንዲሆን ለማድረግ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮችና ቦርዱ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘንድሮ 80ኛ ዓመት የደፈነው መቻል ስፖርት ክለብ፤ የምስረታ በዓሉን የሚዘክር እና የወደፊቱን የክለቡን ጉዞ መሰረት የሚያጸና 'መቻል ለኢትዮጵያ' በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ መርሐ ግብር አዘጋጅቷል።

ኢዜአ ከስፖርት ክለቡ የቦርድ እና የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ኮሚቴ አባላት ጋር በስፖርት ክለቡ ታሪካዊ አመጣጥ፣ አሁናዊ ቁመና እና ቀጣይ ግቦች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።

የመቻል 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ኮሚቴ አባል የሆኑት ብርጋዴር ጀኔራል አስፋው ማመጫ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ አለኝታ መሆኑን አንስተዋል።


 

መቻል ስፖርት ክለብም በ80 ዓመታት ታሪኩ በሁሉም ስፖርት መስኮች ለሀገር ትልቅ አሻራ እያኖረ መሆኑን ተናግረዋል።

መቻል ሻምበል አበበ ቢቂላን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርት አይነቶች አንጋፋ ስፖርተኞችን ያፈራ፣ በተከታታይ ዓመታት የድል ባለቤት የሆነ፣ በህዝብ ልብ ውስጥ የታተመ ስምና ክብር የነበረው ክለብ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ስፖርት ክለቡ በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ስሙ እንዲለወጥ በመደረጉና ተሳትፎው በመገደቡ የቀደመ ስሙ እና ክብሩ ደብዝዞ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን በመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ውሳኔና በህዝብ ፍላጎት የክለቡ የቀደመ መጠሪያ ስምና ክብር እንዲመለሰ በመደረጉ በአሁናዊ ቁመናው ለዋንጫ ተፎካካሪ ደረጃ መድረሱን ጠቅሰዋል።

ለኢትዮጵያ ስፖርት ትንሳኤ በሚቆጩ የክለቡ የቦርድ አመራሮች በኩል ክለቡ በቀጣይ ከአገር ውስጥ ባሻገር ሀገርን ወክሎ የሚሳተፍ ክለብ ለመሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ የአሸናፊነት ወኔ በክለቡ ውስጥ እንዲሰርጽና መቻልን የኢትዮጵያ ስፖርት እድገት አልኝታ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የመቻል ስፖርት ክለብ የቦርድ አባል የሆኑት ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ መቻል መከላከያ ሰራዊት በ116 ዓመታት ተቋማዊ ታሪኩ ከመሰረታቸው ታሪካዊ ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።


 

መቻል በአትሌቲክስ፣ በእግስ ኳስና በሌሎች የስፖርት ፈርጆች ሁሉ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ አኩሪ ገድል የነበረው ክለብ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ታሪኩን ወደሚመጥን ቁመና ለመመለስ ቦርዱ እየሰራ ነው ብለዋል።

ባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ እንደሚሉት አዲሱ የቦርድ አመራር መቻልን በአምስት ዓመታት ውስጥ በአፍረካ 10 ምርጥ ክለቦች አንዱ የማድረግ ስትራቴጂክ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።

ከሰኔ አንድ እስከ ሰኔ 30 ለአንድ ወር በሚቆይ ዝክረ መቻል 80ኛ ዓመት ክብረ በዓልም የተቀመጠውን የመቻል ራዕዩን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ መርሀ ግብራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።

ሼህ አሊ ሁሴን በበኩላቸው ስፖርት ክለቡ ዘመኑን በዋጀ አግባብ በማደራጀትና ስፖርት ሜዳን ጨምሮ ራሱን በራሱ የሚደግፍበት ገቢ እንዲያመነጭ በማስቻል ሀገርን የሚወክሉ ብቁ ስፖተኞችን የሚያፈራ ክለብ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

80ኛ ዓመት ምስረታ ክብረ በዓል የሚካሄዱ መርሐ ግብሮችም ደጋፊዎችን የሚያበዛበት፣ የቁሳቁስ፣ የገንዘብና የሞራል ድጋፎችን የሚመልስበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የመቻል የቦርድ እና የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅት ኮሚቴ አባላት ስፖርትና ውትድርና የማይነጣጠሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የመቻል መጠናከር ለሀገር ሉዓላዊነት መስዕዋትነት ለሚከፍልው መከላከያ ሰራዊት የስነ ልቦና ግንባታ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

በዚህም መቻልን መደገፍ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የአሸናፊነት ስነ ልቦና ግንባታ የሚበጅ እንዲሁም ለጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ምስረታ መሰረት የሚጥል ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ነው ያነሱት።

መቻልን ማጠናከር የኢትዮጵያን ስፖርት ማጠናከር ነው ያሉት ቦርድ አባላቱ፤ መቻል ከሀገር ባሻገር በውጭ ሀገር ኢትዮጵያን ወክሎ አኩሪ ድል የሚያመጣ ክለብ ይሆናል ብለዋል።

በ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅቶች የፓናል ውይይቶች፣ የጎዳና ላይ ሩጫዎች፣ ስፖርታዊ ውደድሮች፣ እንዲሁም ከውጭ ሀገር እግር ኳስ ቡድን ጋር የሚደረግ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገርም የመቻልን ጉዞ የሚዘክር ባዛር እና ዘጋቢ ፊልሞች ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

መቻል እንደ መከላከያ ሰራዊቱ ሁሉ የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀው፤ ይህን ዕውን ለማድረግም የቦርድ አባላቱ ባለሀብቶችን በማስተባበር ሀብት ማሰባሰብ ስራዎችን እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የመቻልን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የገንዘብ፣ የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ እንደሚሻ ጠቁመዋል።

በዚህም ባለሀብቶችን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ወገኖች ሁሉ የመቻል አባልና ደጋፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

በዝግጅቶቹ የገቢ ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን መቻል ቀጣይነት ያለው ራሱን በራሱ የሚመራ፣ ህዝብና ሰራዊቱ የሚኮራበት ስፖርት ክለብ የማድረግ ስራዎች እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

መቻል የኢትዮጵያ ተምሳሌት በመሆኑ መላው የህብረተሰብ ክፍል በዝክረ መቻል 80ኛ ዓመት ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ፣ በአባልነት መመዝገብና ቀጣይነት ያለው ሁለንተናዊ ድጋፉን በማጎልበት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በሕይወት መስዋዕትነት ሀገር የሚጠብቀውንና የድል ሰራዊት የሆነው የመከላከያ ሰራዊት ተቋም የሆነውን መቻል በመደገፍ የሰራዊቱን ድል አድራጊነት በስፖርት ክለብ መድገም ይጠበቃል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም