ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 787 ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በአውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ መስተንግዶ፣ በንግድና በአውሮፕላን ጥገና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 787 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ስነ- ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ሃላፊ አቶ ረታ መላኩ፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ካሴ ይማም  እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ  ታድመዋል።


 

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ካሴ ይማም በዚሁ ወቅት፤ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው ወደ ስራ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በመጪው ጊዜ በአፍሪካ የአቪዬሽን ሴክተሩ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያድግ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ ብቁ የሰው ሃይል የማፍራት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን አየር መንገድ ግሩፕ በየጊዜው ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እያሰፋ የአውሮፕላን ቁጥር እየጨመረና ብቁ የሰው ሃይል እያፈራ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም