የአየር ትራንስፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እየሰራን ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8/2016 (ኢዜአ)፦የስካይ ላይት ሆቴሎችን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት የአየር ትራንስፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለክልሎች ተላልፈው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው የሚያደርግ ሥምምነት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መፈጸሙ ይታወሳል። 

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ ኬላ ሪዞርት ለማስተዳደር የሚያስችል ውል መፈጸማቸውም እንዲሁ።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ጎን ለጎን ቱሪዝምን ሲያስተዋውቅ መቆየቱን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍም ባለ 5 ኮከብ የሆነውን የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ገንብቶ ወደ ሥራ ካስገባበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የስካይ ላይት ሆቴሎችን በየክልሎች ለመገንባት እቅድ የነበረው ሲሆን አሁን የተገኘው አጋጣሚ ግን እቅዳችንን ''በፍጥነት እንድንተገበር አስችሎናል'' ነው ያሉት።

በመሆኑንም፣ በገበታ ለሀገር ከተገነቡ ፕሮጀክቶች በስካይ ላይት ሆቴል ስር  እንዲተዳደር መደረጉ የአየር ትራፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።

በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአምስት ዘርፍ ማለትም በመንገደኞች፣ በካርጎ በሆቴል፣ በምግብና አገልግሎት በአቪዬሽን ዩንቨርሲቲና በአውሮፕላን ጥገና አገልግሎቶች ዘርፍ  እየሰራ ያለ ተቋም ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም